አዲስ አበባ፤ የካቲት 26/2017(ኢዜአ)፡-የአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል የአገር ኩራት የከተማዋ ተጨማሪ ድምቀት ነው ሲሉ ማዕከሉን የጎበኙ የተለያዩ ከፌዴራል ተቋማት የተውጣጡ ጎብኚዎች ገለጹ።
የአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከልን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የካቲት 23 ቀን 2017 ዓ.ም መርቀው መክፈታቸው ይታወሳል።
ማዕከሉ 40 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን እያንዳንዳቸው ከ 3 ሺህ እስከ 4 ሺህ ሰዎችን የመያዝ አቅም ያላቸው ሁለት ትላልቅ የመሰብሰቢያ አዳራሾችን ይዟል።
ስምንት አነስተኛ እና መካከለኛ የመሰብሰቢያ አዳራሾችን ዘመናዊ ሆቴልን፣ ሪስቶራንቶችን፣ ሾው ሩሞችን፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎችና ሌሎች ልዩ ልዩ አገልግሎት መስጫዎችንም አካቷል፡፡
ይህንን ማዕከል የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጉብኝተውታል።
በጉብኝቱ ወቅት ኢዜአ ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች እንደገለጹት፤ በአገሪቷ በርካታ ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ በፍጥነት እየተከናወኑና እየተጠናቀቁ ናቸው።
የአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል ግንባታ ተጠናቆ በመመረቁ እንዳስደነቃቸው ተናግረዋል።
ማዕከሉን ከጎበኙ አስተያየት ሰጪዎች መካከል ቤዛዊት ታምራት፤ ማዕከሉ ለአገር ኩራት ለከተማው ደግሞ ተጨማሪ ድምቀት መሆኑን ገልጻለች፡፡
ማዕከሉ ለአገር ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዳለው አመልክታ፤ ቱሪስቶች እና ኢንቨስተሮችን ለመሳብ የሚያስችል መሆኑን ጠቁማለች።
ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ እናት ካሳ በበኩሏ፤ ማዕከሉ እንዳስደነቃትና በዚህም እጅግ ኩራት እና ደስታ እንደተሰማት ጠቁማለች፡፡
ማዕከሉ የውጪ ምንዛሬ ምንጭ በመሆን ለአገር ኢኮኖሚያዊ እድገት እና ብልጽግና ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ያላትን እምነትም ተናግራለች፡፡
ሌላው ጎብኚ ታዬ ተረፈ በበኩሉ እንደተናገረው፤ የተሰራው ስራ አገርን የሚያኮራ የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያሳድግ ነው፡፡