ደብረ ማርቆስ፤የካቲት 29/2017 (ኢዜአ)፦የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና የወጣቶችን የቴክኖሎጂ እውቀት በማሳደግ ክህሎታቸው እንዲዳብር በማድረገግ የስራ እድልን ለመፍጠር እንዳገዛቸው የደብረ ማርቆስ ከተማ ወጣቶች ገለጹ።
ወጣቶቹ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ መንግስት ባመቻቸላቸው የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና በመሳተፍ ወቅቱ ከሚጠይቀው ቴክኖሎጂ ጋር በመላመድ እጃቸው ላይ ባለው ስልክ መረጃዎችን በማሰስ ለስራ እድል ፈጠራ ማዋል አስችሏል።
የከተማ አስተዳደሩ ስራና ስልጠና መምሪያ ያዘጋጀውን ስልጠናው ወስደው ከተመረቁ ወጣቶች መካከል ትልቅሰው አንሙት እንዳለችው፥ የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ከቴክኖሎጂ ጋር እንድትላመድ አድርጓታል።
ስልጠናውን ከመውሰዷ በፊት እጇ ላይ ያለውን ስልክ ከመደወልና ፌስቡክ ከመጠቀም የዘለለ እውቀት እንዳልነበራት አስታውሳ አሁን ባገኘችው ስልጠና የተለያዩ ፕሮግራሞችን በመስራትና መረጃዎችን በመፈለግ ለስራ እድል ፈጠራ ለማዋል እንዳገዛት አስረድታለች።
ወጣት ገነት አበባው በበኩሏ፥ የኮደርስ ስልጠና በቴክኖሎጂ ራሷን ለማብቃትና ተጠቃሚ ለመሆን እንዳገዛት ተናግራለች።
ይህን እድል ሌሎች ወጣቶችም በመጠቀም ራሳቸውን ከቴክኖሎጂው ጋር በማስተዋወቅ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከልምዷ አካፍላለች።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ስራና ስልጠና መምሪያ ኃላፊ አቶ መኮንን ሙሉአዳም ለኢዜአ እንደገለጹት፥ ቴክኖሎጂን የታጠቀ ማህበረሰብን በመገንባት ዓለም የደረሰበት የእድገት ደረጃን ለማስተካከል እየተሰራ ነው።
በበጀት ዓመቱ ከ3 ሺህ በላይ ወጣቶች የኮደርስ ስልጠና ለመስጠት ታቅዶ እስካሁን ከ1 ሺህ 300 በላይ ወጣቶች የእድሉ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የታቀደውን የኮደርስ ስልጠና ለማሳካትም በደብረ ማርቆስ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ፣በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ፤ በ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና በከንቲባ ጽህፈት ቤት የግንዛቤ ፈጠራ ስራ እየተካሄደ ነው ብለዋል።
የደብረ ማርቆስ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ መምህር ባንተጊዜ ዘላለም በበኩላቸው፥ የኮደርስ ስልጠናው የወጣቱን የቴክኖሎጂ እውቀት በማሳደግ ተወዳዳሪ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።
ያገኙትን የቴክኖሎጂ እውቀት በመጠቀም በኦንላይን ስራ የመፍጠርና ተቀጥሮ የመስራት እድልን የሚከፍት መሆኑን ተናግረዋል።
በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ዳታሳይንስ፣አንድሮይድ ዲቨሎፐርና ፕሮግራሚንግ ፋንዳሜንታል ላይ በማተኮር የሚሰጠውን ስልጠና ሁሉም ሰው ቢወስድ ለሀገር እድገት መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል።