የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

ማዕከሉ ዕውቀት ለትውልድ ለማሻገር እና ቱሪስትን ለመሳብ ወሳኝ አበርክቶ ይኖረዋል- መምህራን

Mar 10, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ የካቲት 30/2017(ኢዜአ)፦ አዲስ አለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ዕውቀትን ለትውልድ በማሸጋገርና ቱሪስትን ለመሳብ ጉልህ አበርክቶ እንደሚኖረው ማዕከሉን የጎበኙ መምህራን ተናገሩ።

አዲስ አለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከልን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የካቲት 22 ቀን 2017 ዓ.ም መርቀው መክፈታቸው ይታወሳል።

ማዕከሉን በአዲስ አበባ በተለያዩ ትምህርት ቤቶች የሚያስተምሩ መምህራን ዛሬ ጎብኝተዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው መምህራን እንዳሉት ኮንቬንሽን ማዕከሉ የኢትዮጵያ ሀብትና የዕድገት ደረጃ የሚያሳይ ነው።

ሁሉንም በአንድ ቦታ የያዘ መሆኑ ደግሞ ተማሪዎች በየትኛውም ዘርፍ ለመሰማራት እንዲያስችላቸው ምቹ እድልን የይፈጥራል ብለዋል።

በተለይም ሀገር ወዳድ፣ በእውቀት የታነጸና ስነ-ምግባር ያለው ትውልድን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ጉልህ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ከመሆኑ ባሻገር ለእውቀት ሽግግር መሳለጥም አይነተኛ ሚና አለው።

መምህር በላይ አይዳኙም እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ በተለያዩ ዘርፎቸ የሚከናወኑ የልማት ስራዎች ለትውልድ የሚተርፉና ጠቀሜታቸውም የላቀ ነው።

በመሆኑም ማዕከሉን ከመጎብኘት በዘለለ ለውቀት ሽግግር ያለውን አስተዋጽኦ በማጉላት ቀጣዩ ትውልድ በዚህ ረገድ የራሱን ድርሻ እንዲወጣ የሚያነሳሳ ነውም ብለዋል።

መምህር ቴዎድሮስ አስናቀ በበኩላቸው ማዕከሉ ''በእውቀት ላይ የተመሰረተ የግንባታ ጥበብ የታየበትና ለታሰበለት ዓላማ ተገቢውን አገልግሎት መስጠት የሚችል መሆኑን ተመልክቻለሁ'' ሲሉ ገልጸዋል።

ይህም ተማሪዎች በትምህርት ከሚያገኙት እውቀት በተጨማሪ በተግባር እንዲመለከቱ ምቹ እድል በመፍጠር የተሟላ እውቀት ያለው ትውልድን ለመገንባት የሚያግዝ ነው ብለዋል።

ማዕከሉ በሁሉም መስክ የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥና ለትውልድ የሚተላለፍ ትልቅ ሃብት መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ መምህርት እመቤት ምትኩ ናቸው።

መምህር ሞገስ ሃብታሙ እንዲሁ ማዕከሉ ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ ረገድ እንደ ተጨማሪ የቱሪስት መስህብነት የሚያገለግል መሆኑን ጠቁመዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ አክለውም ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን በማድረግ ሒደት ውስጥ ማዕከሉ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸው፤ ትውልዱ በሁሉም ዘርፍ የበለጸገች ኢትዮጵያን እንዲረከብ ምቹ እድል ይፈጥራል ነው ያሉት።

የአዲስ አበባ መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት ድንቅዓለም ቶሎሳ በበኩላቸው ጉብኝቱ በዋናነት መምህራን በመማር ማስተማር ስራቸው ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታን እንዲረዱና ለተማሪዎቻቸው እንዲያስተላልፉ ለማስቻል ታልሞ የተካሔደ ነው ብለዋል።

ማዕከሉ ሁሉንም በአንድ ቦታ ያካተተ መሆኑ ደግሞ በሁሉም መስክ ለተሰማሩ መምህራን ጥሩ አጋጣሚ የሚፈጥር በመሆኑ መምህራኑ ለተማሪዎቻቸው ይህንን ማስረዳትና ማስረጽ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.