ሀዋሳ፤ መጋቢት 1/2017 (ኢዜአ ):-በሲዳማ ክልል ባለሀብቶች የሚያደርጉትን የልማት ተሳትፎ እንዲያጠናክሩ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ በየነ በራሳ ጠየቁ፡፡
በክልሉ ከሚገኙ ባለሀብቶች ጋር በልማትና መልካም አስተዳደር እንዲሁም በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ውይይት ተደርጓል።
አቶ በየነ በራሳ በውይይቱ ላይ እንዳሉት በክልሉ በኢኮኖሚያዊና በማህበራዊ ዘርፎች የህዝቡን መሰረታዊ ፍላጎት ለማሟላት አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው።
በዚህ ሂደትም የባለሀብቶች ተሳትፎ የላቀ መሆኑን አንስተው የክልሉ መንግስት ይህንን ተሳትፎ በማሳደግ ልማትን ለማረጋገጥ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ከሲዳማ ህዝብ የቆየ የመረዳዳት እሴት የመነጨ “ካእላሞ” የተሰኘ የተራድኦ ኢኒሼቲቭ በመቅረፅ ወደ ሥራ መግባቱን ገልፀው ኢኒሼቲቩ አነስተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን መደገፉን አብራርተዋል፡፡
በመድረኩ ከተሳተፉ ባለሀብቶች መካከል አቶ ዘሪሁን ቃሚሶ፤ የክልሉ መንግስት ከባለሀብቱ ጋር በመተባበር የህዝቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሥራዎች እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከክልሉ መንግስትጋር በኢኮኖሚ ዘርፎች፣ በትምህርት፣ በጤናና በሌሎች ማህበራዊ መስኮች በትብብር በመስራት ውጤታማ መሆናቸውን አንስተዋል።
''ከክልሉ መንግስት ጋር ያለንን ትብብር በማጠናከርም ለዜጎች የሥራ ዕድልን የሚያሰፉ ሥራዎችን እንሰራለን'' ብለዋል፡፡
በትምህርት ቤቶች ግንባታ እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ህዝቡን ተጠቃሚ በሚያደርጉ ሥራዎች ላይ መሳተፋቸውን ያነሱት ደግሞ ሌላው ባለሀብት አቶ መስፍን ቂጤሳ ናቸው።
በመንግስትና በባለሀብቱ ተሳትፎ በክልሉ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት የታየባቸው መሆኑን አስረድተው የሚያደርጉትን ተሳትፎ እንደሚያጠናክሩም ተናግረዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የክልሉ መንግስት የስራ ሃላፊዎችና ባለሀብቶች ተሳትፈዋል፡፡