የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ-ቻይና የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር መሳለጥ አበርክቶዋን አጠናክራ ትቀጥላለች -የፕላንና ልማት ሚኒስቴር

Mar 12, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤መጋቢት 2/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣናን ትግበራን በማሳለጥ ለአፍሪካ-ቻይና የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር የጎላ አበርክቶዋን አጠናክራ እንደምትቀጥል የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡


በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ ከቻይና ሚድና ግሩፕ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የአፍሪካ - ቻይናን ትብብር ማጠናከር ላይ ያተኮረ መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡


በመድረኩ ላይ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ በረከት ፍስሀፅዮን፣ የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፈቃዱ ጸጋ፣ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቼን ሀይ እና ሌሎችም እንግዶች ተገኝተዋል፡፡


የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ በረከት ፍስሀፅዮን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በኢትዮጵያና ቻይና መካከል ያለው የረጅም ጊዜ ትብብር በመከባበር እና የጋራ ጥቅሞችን በማስጠበቅ ላይ የተመሰረተ ነው።


ቻይና የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ላይ በመሳተፍ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እያገዘች መሆኑን ገልጸው፤ የደቡብ ደቡብ ጠንካራ ትብብርም የዚህ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


ቻይና 10ኛ የኢትዮጵያ ምርቶች መዳረሻ መሆኗን ገልጸዋል፡፡


በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት 8 ነጠብ 5 ቢሊዮን ዶላር ያስመዘገቡ ሶስት ሺህ 300 የቻይና ፕሮጀክቶች መሰማራታቸውን ጠቅሰው፤ ይሄውም ለ325 ሺህ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል መፍጠሩን አንስተዋል።


በቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲብ የአፍሪካና ቻይና ትብብር እየተጠናከረ መምጣቱን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ በትግበራው ቀዳሚ መሆኗን ገልጸዋል፡፡


ኢትዮጵያ የቻይና- አፍሪካ ፎረም እንዲጠናከር ጥረት እንደምታደርግ አውስተው፤ የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ትግበራን በማሳለጥ ለአፍሪካ-ቻይና የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር የጎላ አበርክቶዋን አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል፡፡


በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቼን ሃይ በበኩላቸው ቻይና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እድገት የምታበረክተው አስተዋጽኦ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡


በኢትዮጵያ አምባሳደር ሆኜ በቆየሁባቸው ጊዜያት የተለያዩ አካባቢዎችን ተዘዋውሬ አይቻለሁ ያሉት አምባሳደሩ፤ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ምቹ እና በእድገት ጎዳና ላይ መሆኗን እንዳዩ ገልጸዋል፡፡


ዘንድሮ የኢትዮጵያና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት 55ኛ ዓመቱን እንደሚያከበር ገልጸው፤የሁለቱን ሀገራት በሁኔታዎች የማይለዋወጥ ስትራቴጂያዊ ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡


ቻይና ንግድ፣ግብርና፣ መሰረተ ልማት እና ማዕድን ዘርፍ በትብብር በመሥራት የአፍሪካ የኢንዱስትሪ አብዮት ለማሳደግ ቁርጠኛ መሆኗን ተናግረዋል፡፡


በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት፣የኢኮኖሚ ዞኖችን በማሳደግ እና ወደ ቻይና የሚገቡ ምርቶችን ታሪፍ በማስቀረት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ማሳደግ እንደሚፈልጉም ገልጸዋል፡፡


በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና እንዲሁም በአህጉሪቱ ሰላም እንዲሰፍን ልማት እንዲፋጠንና ብልጽግና እንዲረጋገጥ ከኢትዮጵያ ብሎም ከአፍሪካ ጋር ያለን ትብብር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.