ባህር ዳር፤ መጋቢት 3/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የመንግስት የልማት ድርጅቶች አዳዲስ አሰራሮችንና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ምርታማነታቸውን ይበልጥ ማሳደግና የክልሉን ኢኮኖሚ ማገዝ እንዳለባቸው የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን(ዶ/ር) ገለጹ።
የክልሉ የመንግስት የልማት ድርጅቶች የ2017 በጀት ዓመት የሰባት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን(ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ የልማት ድርጅቶቹ አዳዲስ አሰራሮችንና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ምርታማነታቸውን ማሳደግና የክልሉን ኢኮኖሚ ማገዝ ይገባቸዋል።
የክልሉን የገቢ አቅም በማሳደግ የህዝቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ላይ ትኩረት አድርገው መስራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
የመንግስት የልማት ድርጅቶች ትርፋማ ለመሆንና ተጨማሪ ኢንቨስትመንቶችን በመክፈት ክልሉን በኢኮኖሚ ልማት ተወዳዳሪ ለማድረግ የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
ባለፉት ወራትም ክልሉ በችግር ውስጥ ሆኖ አብዛኞቹ የልማት ድርጅቶች ጠንክረው በመስራታቸው ትርፋማና ስኬታማ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይም አሁን ያስመዘገቡትን ትርፍ በማሳደግ የክልሉን ልማት ይበልጥ ለማፋጠን ጠንክረው መስራት ይገባቸዋል ነው ያሉት።
የክልሉ የልማት ድርጅቶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ አበባው ጌቴ በበኩላቸው፤ በክልሉ በኮንስትራክሽን፣ በኢንዱስትሪ፣ በግብርናና በአገልግሎት ዘርፎች 12 የመንግስት የልማት ድርጅቶች እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ ብለዋል።
የልማት ድርጅቶቹ በክልሉ የነበረውን ችግር ተቋቁመው ባለፉት ሰባት ወራት ባከናወኑት ተግባር ትርፋማ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ድርጅቶቹ ከኢኮኖሚ ልማት በተጨማሪ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በትምህርትና ሌሎች ማህበራዊ ዘርፎች ላይ በመሳተፍ ሃላፊነታቸውን እየተወጡና ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል እየፈጠሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀሪ ወራትም የእርስ በእርስ የልምድ ልውውጥን በማሳደግ ውጤታማ ተግባራትን እንዲያከናውኑ ይሰራል ብለዋል።
ኮርፖሬሽኑ በመስኖ ግንባታና በመጠጥ ውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ዘርፍ ተሰማርቶ እየሰራ እንደሚገኝ የገለጹት ደግሞ የውሃ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዘመነ ፀሐይ ናቸው።
በተለይ በመጠጥ ውሃ ዘርፍ የህብረተሰቡን የረጅም ጊዜ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠትና ተጠቃሚ ለማድረግ በተለያዩ አካባቢዎች እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ኮርፖሬሽኑ በመስኖ ግንባታና በመጠጥ ውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ እያከናወነ ባለው ሥራም ከ10ሺህ ለሚበልጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠሩንም አስታውቀዋል።
ለአንድ ቀን በተካሄደው የግምገማ መድረክ ላይ የክልሉ የልማት ድርጅቶች የሥራ ሃላፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።