አዲስ አበባ፤ መጋቢት 3/2017(ኢዜአ)፦ የሪል ስቴት ልማትና የማይንቀሳቀስ ንብረት ግብይትና ግመታ አዋጅ ተግባራዊ መሆን በዘርፉ የሚከናወኑ ተግባራት ወጥነት እንዲኖራቸው አቅም እንደሚፈጥር መሆኑን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ በሪል ስቴት ልማትና የማይንቀሳቀስ ንብረት ግብይትና ግመታ አዋጅ አተገባበር ዙሪያ ከክልል የከተማና መሰረተ ልማት ቢሮዎች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሄዷል።
የከተማና መሰረተ ልማት ሚንስትር ዴኤታ ሄለን ደበበ በዚህ ወቅት፤ የሪል ስቴት ልማትና የማይንቀሳቀስ ንብረት ግብይትና ግመታ ተገቢው ትኩረት ሳያገኙ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡
ይህን ተከትሎ በዘርፉ የሪል ስቴት ልማትና የማይንቀሳቀስ ንብረት ግብይትና ግመታ የማህበረሰቡን ፍላጎት ታሳቢ ሳያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
መንግስት ከዘርፉ ማግኘት የሚገባውን ገቢ በአግባቡ እንዳይሰበስብ፣ ስራዎች በመረጃ ላይ የተመሰረቱ እንዳይሆኑ ብሎም እንደ ሀገር ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር በሚሰሩ ተግባራት ላይ ማነቆ ሆኖ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡
ጠንካራ የሆነ አዋጅ ባለመኖሩ እንደ ሀገር የህብረተሰቡን የቤት አቅርቦት ጥያቄ ለመመለስ አዳጋች አድርጎት ጭምር መቆየቱን ጠቅሰዋል፡፡
የዘርፉን ችግር ለመቅረፍ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሪል ስቴት ልማትና የማይንቀሳቀስ ንብረት ግብይትና ግመታ አዋጅ ቁጥር 1357/2017 መፅደቁን አስታውሰዋል።
አዋጁ በውጤታማ ተፈጻሚ እንዲሆን በክልል ያሉ አስፈፃሚና ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ ሚንስትር ዴኤታዋ አሳስበዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ የመንግስት ህንፃዎችና ቤቶች ልማት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ኢብሳ ሙሳ፤ በአዋጁ ዙሪያ ግልፅነትን ለመፍጠር እና ለአተገባበሩ ውጤታማነት ምክክር መደረጉ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
ለአዋጁ ውጤታማነት በዘርፉ የተሰማሩ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ሚና ሊጫወቱ ይገባል ያሉት ደግሞ በሀረሪ ክልል የቤቶች ልማትና የመንግስት ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ የቤት ማስተላለፍና አስተዳደር ዳይሬክተር ሙራድ አልዋን ናቸው።