አዲስ አበባ፤ መጋቢት 5/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን የፓተንት ትብብር ቃልኪዳን ለመፈረም የዝገጅት ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ።
ባለስልጣኑ ፓተንትን በዓለም ዙሪያ በቀላሉ ማስመዝገብ የሚያስችለውን የፓተንት ትብብር ቃል ኪዳን ለማፀደቅ የግብዓት ማሰባሰቢያ ውይይት ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ አካሂዷል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወልዱ ይመስል በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤ ፈጠራን የሚያበረታታ ምቹ የንግድ ከባቢ መፍጠር እና ተወዳዳሪነትን ማሳደግ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ትኩረት ከተሰጣቸው መስኮች ዋነኛው ነው።
በዘርፉ ዓለም አቀፍ ተሳትፎንና ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ባለሥልጣኑ በህግ ማዕቀፍ፣ በአገልግሎት አሰጣጥ፣ ግንዛቤ የማሳደግ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም በጥቅምት 2017 የፓሪስ የኢንዱስትሪያዊ ንብረት ስምምነት እና የማድሪድ ዓለም አቀፍ የንግድ ምልክት ምዝገባ ፕሮቶኮል በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መፅደቁን አስታውሰዋል።
የዓለም የአእምሯዊ ንብረት ድርጅት ከሚያስተዳድራቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች መካከል ወሳኝ የሆነውን የፓተንት ትብብር ቃልኪዳን ለመፈረም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
ቃልኪዳኑ ዓለምን የሚያስተሳስር በተበታተነ ሁኔታ የሚሰጡ የፓተንት ማመልከቻ አቀራረብ ወጥ በመሆነ መንገድ ማቅረብ እንደሚያስችልም ገልፀዋል።
በአመልካቹ ፍላጎት ላይ በመመስረት ቀልጣፋ፣ ጊዜና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ማመልከቻው እንዲመዘገቡ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
ቃልኪዳኑን ለመፈረም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመወያየት ግብዓት የማሰባሰብ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ጠምረው ተናግረዋል።
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የኢኖቬሽን ልማት መሪ ስራ አስፈፃሚ ሰላም ይሁን የፓተንት ትብብር ቃልኪዳን መፈረም የሀገር ውስጥ ስታርታፖች ቀልጣፋ፣ ጊዜና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ማመልከቻውን እንዲያቀርቡ ያስችላል ነው ያሉት።
በውይይቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ኃብት ልማት፣ ሥራ ሥምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላትን ጨምሮ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።