ሀዋሳ፤ መጋቢት 8/2017(ኢዜአ)፡- በሲዳማ ክልል ለ2017/18 የምርት ዘመን ጥቅም ላይ የሚውል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ እየቀረበ መሆኑን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ገለፀ።
የቢሮው ምክትልና የግብርና ግብአት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ለገሰ ሀንካርሶ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ለ2017/18 የምርት ዘመን የሚሆን 300 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እየቀረበ ነው።
እስካሁንም 70 ሺህ ኩንታል ዩሪያና ዳፕ የአፈር ማዳበሪያ የበልግ እርሻ ቀድሞ በሚጀመርባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች እየቀረበ መሆኑን ገልጸዋል።
በሲዳማ ኤልቶ ዩኒየን በኩል በ121 ማሰራጫ ጣቢያዎች የአፈር ማዳበሪያውን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ መደረጉንም ተናግረዋል።
በበጋ መስኖ በአንድ ሄክታር መሬት ላይ ለሚያከናውኑት ልማት ማዳበሪያ ማግኘታቸውን የገለጹት ደግሞ በክልሉ የሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደር ገብሬ ቤሴሬ ናቸው።
የአፈር ማዳበሪያ በበቂ ሁኔታ በማግኘታቸው ለበልግ እርሻ የማሳ ዝግጅት ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።
ሌላው የዚሁ ወረዳ አርሶ አደር በየነ ጣኢሮ በበኩላቸው የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ በማግኘታቸው የበልግ እርሻ ሥራ መጀመራቸውን ተናግረዋል።
በበጋ መስኖ በሁለት ሄክታር መሬት ላይ ያለሙትን ጥቅል ጎመንና ቃሪያ በማንሳት በአሁኑ ወቅት ለበልግ እርሻ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል።