አዲስ አበባ፤ መጋቢት 8/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ የአፍሪካን የኢኮኖሚ ውህደት የሚያሳልጡ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ስራዎች ላይ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች እንደምትገኝ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ገለጹ።
የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን 57ኛው አህጉራዊ የፋይናንስና ምጣኔ ሃብት የሚኒስትሮች ጉባኤ በሚኒስትሮች ደረጃ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በጉባኤው የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ፣ የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸኃፊ ክላቨር ጋቴቴ፣ የአፍሪካ አሕጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ዋና ጸኃፊ ዋምኬሌ ሜኔ እና የዚምባቡዌ የፋይናንስ፣ ኢኮኖሚ ልማትና ኢንቨስትመንት ሚኒስቴር ዋና ጸኃፊ እና ተሰናባቹ የአፍሪካ የፋይናንስ፣ የኢኮኖሚና ልማት ሚኒስትሮች ቢሮ ሊቀመንበር አንድሪው ቡቩምቤ ተገኝተዋል።
በዚሁ ጊዜ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ባስተላለፉት መልዕክት፥ አፍሪካ የኢኮኖሚ ዕድገት ሽግግር ለማድረግ በወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች ብለዋል።
የአፍሪካን ድንበር የለሽ ነፃ የሸቀጥና የአገልግሎት ግብይት መሻት ተስፋን እውን ለማድረግ ከምኞት የዘለለ ስራ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ለረጅም ጊዜያት የአፍሪካ የንግድ ሥርዓት እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮችን ለመፍታት ተጨባጭ እርምጃና ስትራቴጂካዊ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል ብለዋል።
በዚህም ሀገራት የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነትን ከማጽደቅ ባለፈ ወደ ተግባር መለወጥና ስኬታማ ብሔራዊ የትብብር ኮሚቴ አዋቅሮ በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።
የአፍሪካ ሀገራትም የመሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት፣ እሴት የተጨመረበት ምርታማነት፣ የፓን አፍሪካ ምርምር ዕድገት፣ ግልጽና ተገማች የኢንቨስትመንት ማዕቀፍ እና የዲጂታል ኢኮኖሚ አቅምን ማጎልበት እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።
በጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ዕድገት፣ በመሰረተ ልማት ትስስር፣ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በሴቶች ተሳትፎ እና አህጉራዊ የዲጂታል ግብይት ሥርዓት አቅም ማጎልበት ላይ በስፋት መስራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያ የንግድ ውህደት ወሳኝ ሚና የሚጫወቱ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ላይ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን አስታውቀዋል።
ለአብነትም የኢትዮ-ጅቡቲን የሚያስተሳስር የምድር ባቡር መስመር፣ የመንገድ፣ የኤሌክትሪክ፣ የቴሌኮምና የውሃ መሰረተ ልማት ግንባታዎች ለአህጉራዊ የኢኮኖሚ ውህደት ምሳሌ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ከኬኒያ እና ደቡብ ሱዳን ጋር የሚያገናኛትን የድንበር ተሻጋሪ ኮሪደር፣ የንግድና ትራንስፖርት መንገድ መሰረተ ልማት ግንባታም ለአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ትስስር ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
በሌላ መልኩ ኢትዮጵያ ቀጣናዊ የኢንቨስትመንትና የኢንዱስትሪ አቅም የሚሆን ተመጣጣኝ፣ ታዳሽና አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ የኢኮኖሚ ውህደትን ለማሳለጥ እየሰራች ትገኛለች ሲሉም ገልጸዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርክና ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ስራዎችም ለአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ትግበራ ያላትን ዝግጁነት የሚያመላክቱ መሆናቸውን አንስተዋል።
በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ የሚገኘው ጉባዔ “የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራን ማፋጠን፤ አፈጻጸሙን የሚያልቁ ስትራቴጂካዊ እርምጃዎችን መቀየስ” የሚል መሪ ሃሳብ ተሰጥቶታል።