የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ልዩ ዘገባ

በዞኑ እየተከናወነ ያለው የገጠር ኮሪደር ልማት የመሬትና የመንገድ አጠቃቀም እንዲሻሻል እያገዘ ነው

Mar 18, 2025

IDOPRESS

አዳማ፤መጋቢት 8/2017(ኢዜአ)፦በምስራቅ ሸዋ ዞን እየተከናወነ ያለው የገጠር ኮሪደር ልማት የመሬትና የመንገድ አጠቃቀም እንዲሻሻል እያገዘ መሆኑን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አባቡ ዋቆ ገለፁ።


አቶ አባቡ ዋቆ ለኢዜአ እንደገለፁት፥ በዞኑ የገጠር ኮሪደር ልማት በስፋት እየተከናወነ ነው።


የኮሪደር ልማቱ በዞኑ በሉሜ፣ ዱግዳ፣ ቦራ፣ አደአ፣ ጉምቢቹን ጨምሮ በሌሎች ወረዳዎች የገጠር ከተሞችን ባከተተ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።


ህዝቡ ስለ ኮሪደር ልማቱ ጠቀሜታ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው በማድረግ የተጀመረው ስራ ህብረተሰቡን አሳታፊ እያደረገ በእቅዱ መሰረት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አንስተዋል።


እስካሁን በተከናወነው የኮሪደር ልማት ስራ የመሬትና የመንገድ አጠቃቀም እንዲሻሻልና ዘመናዊ እንዲሆን እያገዘ መሆኑን ተናግረዋል።


በኮሪደር ልማቱ የአካባቢውን ውበት ከመጨመሩም ባለፈ ነዋሪዎችን ከትራፊክ አደጋ ለመጠበቅ የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል።


ከመሬት አጠቃቀም አንጻርም የአርሶ አደሩን የመኖሪያ አካባቢ አረንጓዴ፣ውብና ለአኗኗር ምቹ እንዲሆንም አስተዋጽኦ እንዳለው አመልክተዋል።


በዚህም የአርሶ አደሩን የመኖሪያ ቤት ዘመናዊ በማድረግ የሰውና የእንስሳት መኖሪያ እና ማደሪያ እንዲለይ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።


ከገጠር ኮሪደር ልማት ጎን ለጎን አርሶ አደሩ በተፈጠረለት ምቹ ሁኔታ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በወተት ላሞችና ዶሮ እርባታ፣ በዓሣ እርባታ፣ በዓሣማ፣ በንብ ማነብና በሌሎች የሌማት ትፋት ስራዎች እየተሳተፈ መሆኑን ገልጸዋል።


ከመሰረተ ልማት አንጻርም የገጠር ቀበሌዎች የኤሌክትሪክ፣ የፀሃይ እና የባዮ ጋዝ ሀይል ማግኘት እንዲችሉ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፥ ይህም ህብረተሰቡ ከዘመናዊ የአኗኗር ዘይቤ ጋር እንዲለማመድና ራሱን እንዲለውጥ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።


በተጨማሪም የማህበራዊ ተቋማት አገልግሎት በተለይ የጤና፣ የትምህርት፣የውሃ፣የመንገድና ተያያዥ መሰረተ ልማትና አገልግሎቶችን አንድ ላይ እንዲያገኝ የኮሪደር ልማቱ አጋዥ መሆኑንም አንስተዋል።


በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት የተጀመረው የገጠር ኮሪደር ልማት ዓይነተ ብዙ ፋይዳ ያለው ሲሆን የገጠር ኮሪደር ልማት ተግባራዊ እየተደረገ ያለው አስቸጋሪ የነበረውን የአኗኗር ዘይቤ ለመቀየር መሆኑ መገለጹ ይታወቃል።


የኮሪደር ልማቱ አርሶ አደሩ ባህሉንና ወጉን ጠብቆ አካባቢውን ንጹህ፤ ጓሮውንም በዶሮ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በማርና ወተት ምርት የተትረፈረፈ በማድረግ ዘመናዊና ቀላል የአኗኗር ስልት እንዲከተል የሚያደርግ መሆኑ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.