ጎንደር፤መጋቢት 8/2017(ኢዜአ)፦በጎንደር ለከተማ ግብርና ልማት በግብአትነት የሚውል የአፈር ማዳበሪያ አምራቹ በወቅቱ እንዲያገኝ እየተደረገ መሆኑን የከተማው አስተዳደር ግብርና መምሪያ ገለጸ።
የአፈር ማዳበሪያው እየቀረበ ያለው ከከተማ ግብርና ባሻገር በከተማው ስር ለሚተዳደሩ የገጠር ቀበሌዎች አርሶ አደሮች ጭምር መሆኑ ተጠቅሷል።
ከተማ አስተዳደሩ በ2017/18 ምርት ዘመን ለአርሶ አደሩ የአፈር ማዳበሪያን በወቅቱና በፍትሃዊነት ማቅረብ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከአጋር አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
በመድረኩ ላይ የመምሪያው ሃላፊ አቶ አበራ አደባ እንደተናገሩት፥ ለምርት ዘመኑ ለአርሶ አደሩ የሚሰራጨው የአፈር ማዳበሪያ ሙሉ በሙሉ በኩፖን ስርአት የሚመራና በአርሶ አደሩ መሬት ልክ በጥናት በተመሰረተ አግባብ የሚከናወን እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
በከተማው ባለፉት ሰባት ወራት ከ600 ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ በኮንትሮባንድ ሲዘዋወር በመገኘቱ በቁጥጥር ስር ውሎ በአዘዋዋሪዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ የተያዘው ማዳበሪያም ለአርሶ አደሩ መከፋፈሉን አንስተዋል፡፡
በከተማ ግብርናና በገጠር ቀበሌዎች ለሚካሄደው የመኸር እርሻ የግብርና ስራ ከ21 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ቀርቦ ለአርሶ አደሩ ስርጭት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
በምርት ዘመኑ በከተማውና በዙሪያው ገጠር ቀበሌዎች 8 ሺህ 573 ሄክታር መሬት የሚለማ ሲሆን 164 ሺህ ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅም ገልጸዋል፡፡
በከተማው የሚገኘው ጸሃይ ገበሬዎች ህብረት ስራ ዩንየን የሪሶርስ ሞብላይዜሽንና የብድር አስተዳደር ክፍል ሃላፊ አቶ ምህረት ግደይ በበኩላቸው፥ ዩንየኑ የአፈር ማዳበሪያ ስርጭቱን ከህገ ወጥ ዝውውርና ኮንትሮባንድ በጸዳ መልኩ እያሰራጨ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እስካሁንም ከ21 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ በከተማው በተቋቋሙ 7 መሰረታዊ ማህበራት መጋዘን እንዲገባ በማድረግ በከተማው ግብርና የስራ ሃላፊዎች ክትትልና ቁጥጥር ስርጭቱ እየተካሄደ ነው ብለዋል፡፡
በከተማ አስተዳደሩ ስር ከሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች መካከል የክልል እየሱስ ገጠር ቀበሌ ግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ታፈረ ብርሃኑ በማህበራት በኩል ለመኸር እርሻ የሚውል 3 ሺህ 249 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ቀርቦ በወቅቱና በፍትሃዊነት ለአርሶ አደሩ እየተሰራጨ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩንየን የስራ ሃላፊዎች አበዳሪ ድርጅቶች የፍትህና የፖሊስ ተቋማት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡