አዲስ አበባ፤ መጋቢት 8/2017(ኢዜአ)፦ በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበው ከኒው ዴቨሎፕመንት ባንክ ፕሬዝዳንት ዲልማ ሩሴፍ ጋር ዛሬ በቻይና ሻንጋይ ከተማ ተወያይተዋል።
ውይይቱ ኢትዮጵያ የባንኩ አባል ለመሆን ያቀረበችው ጥያቄ ያለበት ደረጃ እና የሁለቱ ወገኖች የጋራ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑን በቤጂንግ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።
ኒው ዴቨሎፕመንት ባንክ (በቀድሞ አጠራሩ የብሪክስ ልማት ባንክ) በብሪክስ አባል ሀገራት እ.አ.አ በ2014 ተቋቁሞ ከአንድ ዓመት በኋላ በ2015 ወደ ስራ መግባቱ ይታወቃል።
ግዙፉ የባለብዝሃ ወገን የልማት ባንክ ስምንት አባል ሀገራት አሉት።
ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ቻይና፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ባንግላዴሽ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ግብጽ የባንኩ አባል ሀገራት ናቸው።