የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ልዩ ዘገባ

ሴቶች እምቅ የፈጠራ አቅማቸውን በመጠቀም ለሀገር ዕድገት ሚናቸውን እንዲወጡ እየተሰራ ነው - የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር

Mar 19, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 9/2017(ኢዜአ)፡- ሴቶች እምቅ የፈጠራ አቅማቸውን በመጠቀም ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን በመፍጠር ለሀገር ዕድገት ሚናቸውን እንዲወጡ አዳዲስ መርሐ ግብሮች ተቀርጸው እየተተገበሩ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሰሎሞን ሶካ አመለከቱ።

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር "ብሩህ እናት" የተሰኘ የሴት ኢኖቬተሮች የፈጠራ ሃሳብ ውድድር የቡት ካምፕ ስልጠና ማስጀመሪያ መርሃ ግብር አካሂዷል።


የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሰለሞን ሶካ በመርሃ ግብሩ ማስጀመሪያ እንደገለጹት፤ ሚኒስቴሩ በኢትዮጵያ የቴከኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ አዳዲስ ቴክኖሎጂ የሚያመነጩና የፈጠራ ሃሳብ ያላቸውን ወጣቶች የሚደግፉ መርሐ ግብሮችን እየቀረጸ ነው።

በተጨማሪም አዳዲስ አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ እምቅ አቅምና ችሎታ ያላቸውን ታዳጊዎችና ወጣቶች ለመደገፍ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ችግር ፈቺ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸው ወጣቶች ሃሳባቸው ወደ ተግባር ተቀይሮ ተጨባጭ ውጤት እንዲያስገኝ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ለዚህም “ማሰልጠን፣ መሸለም እና ማብቃት” በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደው “ብሩህ ኢትዮጵያ” ሀገር አቀፍ የቢዝነስ ፈጠራ ሃሳብ ውድድር ተጠቃሽ መሆኑን አመልክተዋል።

ሴት ተወዳዳሪዎች ይዘዋቸው የቀረቡት የፈጠራ ስራዎች ችግር ፈቺ እና ጉልህ ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸው እንደሆኑም ጠቅሰዋል።

በዚህም ሴቶች የፈጠራ አቅማቸውንና ከስልጠናው የሚያገኙትን እውቀት በመጠቀም በሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የበኩላቸውን እንዲወጡ እየተሰራ ነው ብለዋል።


በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሴቶች ፕሮግራም አናሊስት ስመኝ ኩማ በበኩላቸው፤ ሴቶች የፈጠራ ችሎታና አቅማቸውን አሳድገው የተሻለ ቦታ መድረስና ለሌሎች የስራ እድል መፍጠር እንደሚችሉ ገልፀዋል።

ሰልጣኞቹ በላቀ ስራ ሌሎች ሴቶች ወደ ቴክኖሎጂው ዘርፍ እንዲሳቡ አርአያ መሆን እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።


የእናት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ትግስት አባተ በበኩላቸው፤ ባንኩ ካሁን ቀደም ሴቶች የብድር ዋስትና አግኝተው በቢዝነስ ሃሳባቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ድጋፍ እንደሚያደርግ አንስተዋል።

ወደ ስልጠና የገቡት ሴት የፈጠራ ባለሙያዎችም የፈጠራ ስራቸው መሬት ወርዶ ህልማቸውን እውን እንዲያደርጉ ባንኩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።


የስልጠናው ተሳታፊ የሆነችው ሴት የፈጠራ ባለሙያዋ ማርታ ጁቤ፣ ስልጠናው አቅሟን በመጠቀም ግቧን እንድታሳካ የሚያስችል መሆኑን ነው የተናገረችው።


ብዙ ልምድና አቅም ባላቸው አሰልጣኞች የሚሰጣቸው ስልጠና ለወደፊት የፈጠራ ጉዞዎቿ እንደሚያግዛቸው የገለጸችው ደግሞ ሊድያ አለማየሁ ናት።


ናርዶስ ተስፋዬ በበኩሏ ስልጠናው የፈጠራ ስራዎቻቸውን ለማዳበር ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው አንስታለች።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.