አዲስ አበባ ፤ መጋቢት 9/2017 (ኢዜአ)፦ በመንገድ ዘርፍ የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ሁሉን አቀፍ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለጹ።
የመንገድ ዘርፍ አፈጻጸም ላይ የሚታዩ ተግዳሮቶች እና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሄዷል።
የኢትዮጵያ የመንገድ ሽፋን የመንገድ ዘርፍ ልማት ፕሮግራሙ በ1989 ዓ.ም ከነበረበት 23 ሺህ ኪሎ ሜትር አሁን ላይ ወደ 171 ሺህ ማድረስ መቻሉ ተገልጿል።
የግንባታ ግብዓት ዋጋ መናር፣ የወሰን ማስከበር፣ የመንገድ ጥገና ላይ ያሉ ክፍተቶች (የማሽነሪ እና የባለሙያ እጥረት) እና የፕሮጀክት አመራር እና የሀገር በቀል የሥራ ተቋራጮች ያሉ ውስንነቶች የዘርፉ ማነቆዎች መሆናቸው በውይይቱ ላይ ተነስቷል።
የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በመንገድ ዘርፍ ያሉ ተግዳሮቶችን በአፋጣኝ መፍታት ልዩ ትኩረት እንደሚያሻው አመልክተዋል።
የወሰን ማስከበር ሥራዎችን በታቀደ መልኩ መፈጸም፣ የመንገድ ጥገናን በተቀመጠለት ጊዜ ማጠናቀቅ ማጠናቀቅ፣ የሰው ኃይል አቅም ግንባታ እና የግሉ ዘርፍ በመንገድ ግንባታ ያለውን ድርሻ ማሳደግ እንደሚገባ አመልክተዋል።
ሚኒስቴሩ ለመንገድ ዘርፍ አፈጻጸም መሻሻል አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር መሐመድ አብዱራህማን (ኢ/ር)፤ በመንገድ ዘርፍ ያሉ ውጤቶች ለማስቀጠል እና ተግዳሮቶቹን በዘላቂነት ለመፍታት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የዘርፉን ውጤታማነት ሁሉን አቀፍ ጥረት እና የባለድርሻ አካላት የጋራ ጥረት ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።
የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ከውይይቱ በተጨማሪ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የመንገድ ምርምር ማዕከልን መጎብኘታቸውን ከአስተዳደሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።