የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ልዩ ዘገባ

ከተሞችን ያነቃቃው የኮሪደር ልማት - የጭሮ ኮሪደርን በጨረፍታ

Apr 3, 2025

IDOPRESS

የጭሮ ወተት ገበያ ከከተማው ዋና መንገድ ግራና ቀኝ የሚካሄድ የተጨናነቀ ገበያ ነው፡፡ በዚህ ስፍራ በርካቶች ከማለዳ እስከ ማታ ገዥና ሻጮች ይገናኙበታል። የዚሁኑ የገበያ ማእከል እንቅስቃሴ ለመቃኘት የኢዜአ ሪፓርተር ወደ ስፍራው ባቀናበት ወቅት በገበያው ግራና ቀኝ በመንገዱ ዳርቻ ቁፋሮ እየተከናወነ ሲሆን ግብይቱም ሞቅ ደመቅ እንዳለ እንደቀጠለ ነው።

በገበያው አመሻሽ ላይ ወተት እየሸጡ ካገኘቸው መካከል ወይዘሮ ሳርቱ አሊ፤ በአካባቢው የኮሪደር ልማቱን ተከትሎ የመንገድ ስራው ሌት ተቀን የሚከናወን በመሆኑ የወተት ገበያው በምሽትም በርካታ ተጠቃሚዎች ስላሉት ለመሸጥ መገኘታቸውን ነገሩን።

ከዚህ በፊት በተለይም በምሽት ገበያው ቀዝቀዝ ያለ እንደነበር አስታውሰው የኮሪደር ልማቱ ከተጀመረ ግን በየቀኑ በምሽት አራት ጀሪካን ወተት ሽጠው የሚመለሱ መሆኑን ጠቅሰው ''ልማቱ ስራም ገበያም ፈጥሮልናል'' ይላሉ። በጭሮ ከተማ ምሽት ጭምር የሚደራው የወተት ገበያ ከአስር ብር ጀምሮ በመግዛት የሚጠቀሙ መሆኑን ሸማቾችም ይናገራሉ።

በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች ለበርካቶች የስራ እድል መፍጠራቸው እንዳለ ሆኖ በጥራትና በፍጥነት እየተከናወኑ ይገኛሉ። በመሆኑም ከዚህ በፊት ይስተዋሉ የነበሩ የፕሮጀከቶች መጓተት ችግር የተፈታበትና ሌት ተቀን የሚሰራበትን የስራ ባህል የፈጠረ መሆኑን ለማየት ችለናል። የኮሪደር ልማት ስራው በአጭር ጊዜ በጥራት ለማከናወን እየተደረገ ያለው የመንግስት የስራ አመራር እና በባለሙያዎች ጥረትም የሚደነቅ ነው።

በጭሮ የኮሪደር ልማት በማህበር ተደራጅተው እየሰሩ ካሉ የዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች መካከል ወጣት ጀማል ኑሬ እና አምስት ጓደኞቹ በኮሪደር ልማቱ የስራ ዕድል አግኝቷል፡፡ የኮሪደር ልማቱ ከስራ ዕድል ፈጠራም በላይ በዩኒቨርሲቲ የቀሰሙትን የምህንድስና ትምህርት በተግባር ለመፈፀም ያስቻላቸው መሆኑን ይናገራል፡፡

የኮሪደር ልማት ስራ ከዚህ ቀደም ሲከናወኑ ከነበሩት የመሰረተ ልማት ስራዎች የሚለየው በመንገዶች ግራና ቀኝ የሚከናወኑ የውበት ስራዎች እንዲሁም ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎችን ታሳቢ ያደረገ የእግረኛ መንገድ፤ የአደባባይ የድልድይና የመሳሰሉ ተዛማጅ ስራዎች በአንድ ላይ መያዙ ነው፡፡

በዚህም ከተማን ከማዘመን እና ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በእኩል ደረጃ ተጠቃሚ ማድረጉ ኮሪደር ልማቱ ልዩ ጠቀሜታዎች ናቸው፡፡

''የኮሪደር ልማት ስራው ሲጠናቀቅ እኔም ሙሉ ልምድና ዕውቀት አዳብሬ እወጣለው'' ያለው ወጣቱ ከገቢ በተጨማሪ እንደ ልምድ ማካበቻ እና መማሪያ በማየት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሆነ ይገልጻል፡፡

ከጨርጨር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በሰርቬይንግ ሙያ የተመረቀው የሱፍ ቀመር በኮሪደር ልማቱ የስራ ዕድል ተጠቃሚ የሆነው ሌላኛው ወጣት ነው፡፡ የኮሪደር ልማት በርካታ ስራዎች በአንድ ላይ የሚከናወንበት በመሆኑ ከሙያው በተጨማሪ ሌሎች ሙያዎችንም ለመቅሰም ያስችለዋል፡፡

የከተማው ነዋሪዎችም የኮሪደር ልማቱን ጠቀሜታ ከዚህ ቀደም ከነበሩት ችግሮች ጋር በማያያዝ ይገልጹታል፡፡ ጭሮ ከተማ ከአዲስ አበባ ድሬዳዋ ጅቡቲ የሚጓዙ ተሸከርካሪዎች የሚተላለፉባት ከተማ በመሆኗ የመንገዱ ጥበት ከትራፊክ መጨናነቅ ጋር ተያይዞ ለእንቅስቃሴ አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡

በአሁኑ ወቅት በከተማው ተጀምሮ እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት መንገዱን በእጥፍ እያሰፋው በመሆኑ የትራፊክ ፍሰቱን የተሸለ ከማድረግ ባለፈ የኢኮኖሚ እንንቅስቃሴውንም በመጨመር ከተማዋን የሚያነቃቃ ነው ይላሉ በከተማው የቡርቃ ጭሮ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ከድር እስማኤል፡፡

የኮሪደር ልማቱ ዕድሜ ጠገቧን ጭሮ ዳግም ወደ ቀድሞ ውበቷ እንደሚመልሳት ተስፋ አላቸው፡፡ ጭሮ ከተማ አሁን ቀን ወጥቶላታል የሚሉት አቶ ከድር ከዚህ በላይ ለከተማዋ የሚያስደስት ነገር ባለመኖሩ በተጠየቁት ሁሉ ልማቱን ለማገዝ ዝግጁ እንደሆኑም ተናግረዋል፡፡

የጭሮ ከተማ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ጀማል ጎሳዬ እንዳሉት በከተማው የተጀመረው የኮሪደር ልማት እነዚህን ሁለት ዋና የአስፋልት መንገዶች ስፋት በእጥፍ በማሳደግ ወደ 40 ሜትር ከፍ የማድረግ ዓላማ አለው፡፡

ይህም የከተማዋዉን የትራፊክ እንቅስቃሴ ከማሳለቱም በላይ ለፈጣን የንግድ እንቅስቃሴውም የጎላ ፋይዳ ይኖረዋል ይላሉ፡፡

በከተማው የተጀመረው የኮሪደር ልማት በከተማው ለሚገኙ ወጣት ባለሙያዎች ሙያቸውን የሚያዳብሩበት እና በልማቱ ለተሰማሩ ሌሎች ግለሰቦች የስራ ዕድል የተፈጠረበት በተጨማሪም በጥቃቅን የመንገድ ዳር የምግብ አገልግሎት ለሚሰጡ ነዋሪዎች ከፍተኛ ጠቀሜታ እየሰጠ ነው፡፡

ከሁሉም በላይ ደግሞ ከተቆረቆረች ረጅም አመት ላስቆጠረችውና ለደከመችው ከተማ ዳግም መነቃቃት የፈጠረ እና የከተማዋን እምቅ ኢኮኖሚ በማንሰራራት ረገድ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ነዋሪዎቿ ገልጸዋል፡፡

የጭሮ ከተማ ከአዲስ አበባ እስከ ጅቡቲ ድረስ የሚጓዙ አሽከርካሪዎች ለማረፍ የሚመርጧት ከተማ በመሆኗም ልማቱ ሲጠናቀቅ ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኝላት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

ለዚህም በከተማው ተጀምሮ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ዘርፈ ብዙ እና የከተማዋን ተስፋ ያለመለመ ተስፋ ሰጪ ጅምር ነው፡፡

ለዚህ ነው ወይዘሮ ሳርቱ አሊ እና ሌሎች የጭሮ ከተማ ነዋሪዎች የኮሪደር ልማቱን ለማገዝ የሚችሉትን ሁሉ ለመወጣት የተዘጋጁት።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.