የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ልዩ ዘገባ

በክልሉ ለኢንዳስትሪ ዘርፍ የተሰጠው ትኩረትና የሚደረገው ድጋፍ አምራች ኢንዱስትሪውን ውጤታማ እያደረገው ነው

Apr 3, 2025

IDOPRESS

ዲላ፤ መጋቢት 24/2017(ኢዜአ)፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለኢንዳስትሪ ዘርፍ የተሰጠው ትኩረትና የሚደረገው ድጋፍ አምራች ኢንዱስትሪውን ውጤታማ እያደረገው መሆኑ ተገለጸ።

በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግና ከውጭ የሚገባውን ምርት በሀገር ውስጥ ለመተካት በተከናወነው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተሳካ ውጤት መገኘቱ ይታወቃል።

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የነበረው እንቅስቃሴም የአምራች ኢንዱስትሪውን ማነቆዎች በመፍታት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ያስቻለ መሆኑን የዘርፉ ተሳታፊዎች ተናግረዋል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን ከሰጡ የአምራች ኢንዱስትሪዎች ኃላፊዎች መካከል በደቡብ ኦሞ ዞን በናፀማይ ወረዳ የናሳ ብራይሌ እርሻ ልማት ድርጅት የጥጥ መዳመጫ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ አቶ እስጢፋኖስ ወልደሚካኤል እንዳሉት ፋብሪካው ጥጥ ላይ እሴት በመጨመር ለሀገር ውስጥ ጨርቃጨርቅና ዘይት ፋብሪካዎች እያቀረበ ነው።

መንግስት ለኢንዱስትሪው በሰጠው ትኩረት የተሳለጠ የእሴት ሰንሰለት በመፈጠሩ ምርቱ በፍጥነት ለገበያ እየቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።

በጋሞ ዞን አርባ ምንጭ ከተማ ቤሪ ሐር ልማት ኃላፊነቱ የተሰወነ የግል ድርጅት ስራ አስኪያጅ አቶ ገለታ ሃይሉ በበኩላቸው ድርጅታቸው በሐር ልማት ላይ በመሰማራት ምርቱን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እያቀረበ ነው።

የለውጡ መንግስት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በመሬት አቅርቦት፣ በካይዘን፣ በምርት ጥራትና ብክነት ቅነሳ የተለያየ ድጋፍና ስልጠና በመስጠቱ ውጤታማ አድርጎናል ብለዋል።

ድርጅቱ የመንግስት ድጋፍ የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በቀጣይ ከውጪ የሚገቡትን ምርቶች በሚተኩት ላይ ለማተኮር ማቀዱን ተናግረዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ቦጋለ ቦሼ(ዶ/ር) በበኩላቸው የለውጡ መንግስት ብዝሃ የኢኮኖሚ ዘርፎችን መከተሉ ለክልሉ የኢንዳስትሪ ልማት እድገት መሰረትን የጣለ ነው።

በዚህም የጎጆ ኢንዱስትሪዎችን ጨምሮ በክልሉ የሚገኙ ከ1ሺህ 250 በላይ ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ለማሻሻል ማነቆዎችን የመፍታት ስራ በትኩረት መከናወኑን ገልጸዋል።

በተያዘው ዓመትም በክልሉ የሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅምን በ13 በመቶ ማሳደግ መቻሉን ጠቁመዋል።

በዚህም ከ8 ነጥብ 7 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ተኪ ምርት እንዲሁም ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር በላይ እሴት የተጨመረባቸውን የግብርና ምርቶች ወደ ውጭ መላክ መቻሉን ገልጸዋል።

በእሴት ሰንሰለቱም ከ1ሺህ ለሚልቁ ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩን ጠቅሰው ይህም የለውጡ ትሩፋት መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.