የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ልዩ ዘገባ

ባለፉት የለውጥ አመታት በትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ዘርፍ ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቧል - ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር)

Apr 3, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤መጋቢት 24/2017 (ኢዜአ)፦ባለፉት ሰባት የለውጥ አመታት በተከናወኑ ተግባራት በትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ዘርፍ አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለፁ።

ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሳል አመራር ባለፉት ሰባት የለውጥ ዓመታት ያጋጠሙ ፈተናዎችን እያሸነፈች ትልልቅ ስኬቶችን ማስመዝገቧን ተናግረዋል።

“ትላንት ዛሬ ነገ ለኢትዮጵያ ልዕልና” በሚል መሪ ሀሳብ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተገኙ ውጤቶች እንዲሁም በቀጣይ ስራዎች ላይ የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት ሰራተኞች ውይይት አድርገዋል።


በመድረኩ የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ(ዶ/ር)፤ ሚኒስትር ዴኤታ በርኦ ሀሰንን ጨምሮ ከፍተኛ አመራሮችም ተገኝተዋል።

ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት የለውጥ ዓመታት በሁሉም ዘርፎች ስኬቶችን አስመዝግባለች።

በዚህም በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በማህበራዊና በዲፕሎማሲ ዘርፎች ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ መቻሏን ተናግረዋል።

ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የሰጡት በሳልና አሻጋሪ አመራር ኢትዮጵያ ፈተናዎችን እያሸነፈች ትልልቅ ስኬቶችን እንድታስመዘግብ አድርጓታል ብለዋል።

ከዚህም መካከል በትራንስፖርት ዘርፉ ከለውጡ በኋላ የተለያዩ ሪፎርሞችን በማካሄድ የአየር፣ የባቡር፣ የመንገድ ትራንስፖርት እንዲሁም በሎጄስቲክ ዘርፍ ስኬቶች መመዝገባቸውን ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡

በዘርፉ በርካታ ስኬቶች ቢመዘገቡም አሁንም ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ለዚህም በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ በሚሰራው ስራ የትራንስፖርት ሚኒስቴርን ጨምሮ የተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሰራተኞች በተሰማሩበት ዘርፍ ይበልጥ መትጋት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።


የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በርኦ ሀሰን በበኩላቸው በለውጡ አመታት በትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ዘርፉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ መስራቱን ተናግረዋል።

በዚህም ሎጀስቲክስ የማንሳት አቅም በከፍተኛ መጠን ያደገበት፣ የአየርና የባቡር ትራንስፖርት ዘርፎችም ለውጥ ያስመዘገቡበት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

እንዲሁም የደረቅ ወደቦችንና የሞዳል ትስስርን በማሳለጥ ረገድ የተሰራው ተግባር ከፍተኛ ለውጥ የተመዘገበበት መሆኑን ገልጸዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎቹ መካከል ፔጥሮስ ወልደ ሰንበት እና ሀና ሞገስ በሰጡት አስተያየት ለውጡን ተከትሎ በትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ የተሰሩ ስራዎች አገሪቷን በኢኮኖሚ በማህበራዊ እና በፖለቲካው ዘርፎች ተጨባጭ ለውጥ እንድታስመዘግብ ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡

ተሳታፊዎቹ እየተመዘገበ ያለው ዘርፈ ብዙ ለውጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በተሰማሩበት ዘርፍ ጠንክረው እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.