አዲስ አበባ፤ መጋቢት 27/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ያመጠቀቻቸው ሁለት ሳተላይቶች ያመነጯቸው መረጃዎች ለኢኮኖሚ ዕድገት የላቀ ፋይዳ እያበረከቱ እንደሚገኝ የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ኢትዮጵያ ETRSS-1’ እና ኢቲ ስማርት አር ኤስ ኤስ (ET-Smart-RSS) የተሰኙ ሁለት የመሬት ምልከታ ሳተላይቶችን ማምጠቋ የሚታወስ ነው።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አብዲሳ ይልማ እነዚህ ሳተላይቶች ወደ ህዋ ከመጠቁ በኋላ በርካታ ጥቅም እያስገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሳተላይቶቹ ለግብርና፣ ለደንና አየር ንብረት ጥበቃ፣ ለማዕድን፣ ለተፈጥሮ ሀብት ጥናትና መረጃ ለመሰብሰብ እንዲሁም ለመሰረተ ልማት ዝርጋታ የሚሆኑ ጥራት ያላቸው መረጃዎችን መላካቸውን ተናግረዋል።
ኢንሰቲትዩቱ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሀይል እንዲኖር ለማስቻል ከዩንቨርሲቲዎች ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
እንዲሁም የልጆች የስፔስ ክህሎት ማእከል በማቋቋም በክረምት ወራት ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ታዳጊዎች እያሰለጠነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂም የቅንጦት ሳይሆን ኢትዮጵያ ተወዳዳሪና ውጤታማ እድገት ለመፍጠር አጋዥ ዘርፍ መሆኑን አብራርተዋል።
የነዚህን ሳተላይቶች መረጃ በመጠቀም ለኢኮኖሚያዊ እድገቱ መረጋገጥ የላቀ ፋይዳ ያላቸው ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አመላክተዋል።
ኢንስቲትዩቱ 3ተኛዋን ሳተላይት ለማምጠቅ የመጀመሪያ ምእራፍ መጠናቀቁን ገልጸው ይህም ከፍተኛ የምስል ጥራት ያለው ሳተላይት መሆኑን ተናግረዋል።
በኢንስቲትዩቱ የካርታ ስራ መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ቴዎድሮስ ካሳሁን በበኩላቸው በነዚህ ሳተላይቶች የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር፣ የችግኝ ማፍያ እና መትከያ ቦታዎችን በሚመለከት የጂኦስፓሻል መረጃዎችን መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል።
ሳተላይቶቹ የውሃ አካላትን መረጃዎች ለመተንተን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳስገኙ የገለጹት ደግሞ በኢንስቲትዩቱ የዲጂታል ኢሜጅ ፕሮሰሲንግ መሪ ስራ አስፈጻሚ ተስፋዬ ዳኜ ናቸው።
በተመረጡ ሃይቆች ላይ መረጃዎችን በመሰብሰብ እና በመተንተን ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተደራሽ እየሆኑ መሆኑንም አመላክተዋል።