አርባ ምንጭ፤ መጋቢት 27/2017(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል "ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት" በሚል መሪ ሃሳብ አውደ ርዕይና ባዛር በአርባ ምንጭ ከተማ ዛሬ ተከፍቷል።
በአውደ ርዕዩና ባዛሩ ላይ ከ60 በላይ መካከለኛ፣ አነስተኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ምርቶቻቸውን አቅርበዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ፣ የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አዳማ ትንጳዬ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቦጋለ ቦሼ እና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ አመራር አባላት አውደ ርዕይና ባዛሩን ከፍተዋል።
ዓላማው የኢንዱስትሪ ዘርፍ ለሀገር ኢኮኖሚ ያለውን ሚና ለማላቅና ተኪ ምርቶች በጥራትና በስፋት እንዲመረቱ በማድረግ የውጭ ምንዛሬን ለማዳንና ለማስገኘት እንደሆነም ተመላክቷል።
በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የመጡ ለውጦችና ቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ ውይይት እንደሚደረግም ከመርሃ ግብሩ መረዳት ተችሏል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የፌዴራል፣ የክልል፣ የጋሞ ዞን እና የአርባ ምንጭ ከተማ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።