አዲስ አበባ፤ መጋቢት 27/2017 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ እስካሁን ከስድስት መቶ በላይ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ መመለሳቸውን የአምራች ኢንዱስተሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሚልኬሳ ጃጋማ(ዶ/ር)ገለጹ።
የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች በአዲስ አበባ እና ኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተሞች በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተጨባጭ ውጤት ያስመዘገቡ ኢንዱስትሪዎችን ጎብኝተዋል።
የጉብኝቱ አላማ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ወደ ስራ የተመለሱ ኢንዱስትሪዎችን የስራ እንቅስቃሴ ለመመልከት ያለመ መሆኑ ተመላክቷል።
የኢትዮጵያ አምራች ኢንዱስተሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሚልኬሳ ጃጋማ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም በጉልህ አሳድጓል።
ንቅናቄው ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት፣ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በጥራትና በብዛት በማምረት ከፍተኛ ውጤት እንዲመዘገብ ማስቻሉን ጠቁመዋል።
በንቅናቄው በተፈጠሩ ቅንጅታዊ አሰራሮች የዘርፉን ማነቆዎች በመለየት ተዘግተው የነበሩ ኢንዱስትሪዎች ወደ ምርት መመለሳቸውን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ እስካሁን ስድስት መቶ ሃያ አምስት የሚጠጉ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ መመለሳቸውንም አክለዋል።
ከንቅናቄው በፊት የነበረው የማምረት አቅም 48 በመቶ እንደነበር ገልጸው በንቅናቄው አማካኝነት አሁን ላይ የማመረት አቅም 61 ነጥብ 08 በመቶ መድረሱን አመላክተዋል።
እንዲሁም ከዚህ ቀደም የአምራች ዘርፉ የሚመራበት ፖሊሲ እንዳልነበር አስታውሰው፤ በዚሁ ንቅናቄ ዘርፉ የሚመራበት አዲስ ፖሊሲ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
ከፖሊሲው በመነሳትም የዘርፉን ችግሮች የሚፈቱ በርካታ ስትራቴጂዎች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
የዘደይ አግሮ ኢንዱስተሪ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ስራ አስኪያጅ የዚችአለም ካሳ ንቅናቄው በህብረተሰቡ ውስጥ የሀገር ውስጥ ምርት ተጠቀሚነት እንዲያድግ ጉልህ አስተዋጽኦ ማድረጉን ተናግረዋል።
እንዲሁም ከዚህ ቀደም ከውጭ የሚገቡ ምርቶች በሀገር ውስጥ እየተመረቱ ነው የሚለውን ግንዛቤ መፍጠር የቻልንበት ነው ሲሉም አስታውቀዋል።
የ ቢ ኤም ኤፍ የባህልና ዘመናዊ አልባሳት ማምረቻ ስራ አስኪያጅ ማርስአለም ሁሴን በበኩላቸው፤ ንቅናቄው ከተኛንበት ያነቃን ነው ብለዋል።
የማምረት አቅማቸው እንዲያድግ እንዲሁም በስራ እድል ፈጠራ ላይ የነበራቸው አስተዋጽኦ ከፍ እንዲልም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።
በንቅንቄው የተፈጠረው ቅንጅታዊ አሰራር ማነቆዎችን እየፈታልን ነው ያሉት ደግሞ የአዳኣል ኢንዱስትሪያል ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ስራ አስኪያጅ አዳነ በርሄ ናቸው።
የኬርኤዢ የቆዳ ውጤቶች ማምረቻ ስራ አስኪያጅ ዘላለም መርአዊ በየአመቱ የሚካሄደው ኤክስፖ ከፍተኛ መነቃቃት መፍጠሩን ገልጿል።
እንዲሁም የእርስ በእርስ ትውውቅና እና የገበያ ትስስር እንዲጎለብት ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከተን ተናግሯል።
የእጅግ ጥበብ ስራ አስኪጅ እጅጋየሁ ሀይለጊዮርጊስም ንቅናቄው በተለያዩ ኤግዚቢሽኖች ምርታቸውን ለማስተዋወቅ እድል እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።
እንዲሁም በንቅናቄው አማካኝነት እየተደረገ ያለው ድጋፍ መልካም መሆኑንም ነው የተናገሩት።