አክሱም፤ መጋቢት 27/2017(ኢዜአ)፦ መሬታቸውን በበጋ መስኖና በመኸር እርሻ ማልማት መቻላቸው በግብርና ምርታቸው ተጠቃሚ መሆናቸውን በትግራይ ክልል ማዕከላዊ ዞን የላዕላይ ማይጨው ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ።
አርሶ አደሮቹ በመጪው የመኸር ወቅት የተሻለ ምርት ለመሰብሰብ የሚያስችላቸውን ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በወረዳው የ"ድራ" ገጠር ቀበሌ ነዋሪ ሴት አርሶ አደር አበባ ገብረክርስቶስ እንዳሉት፣ በበጋ ለመስኖ ልማት ሲጠቀሙበት የነበረውን ማሳ ምርቱን በማንሳት ለመኸሩ አዝመራ የምንጣሮ ስራ በማከናወን ደጋግመው በማረስ አዘጋጅተዋል።
በምርት ዘመኑ የተሻለ ምርት ለመሰብሰብ ሁለት ኩንታል ዘመናዊ ማዳበሪያ ከገበሬዎች የህብረት ስራ ማህበር ገዝተው ያዘጋጁ ሲሆን፣በተጓዳኝም ከተፈጥሮ ፍግ፣ ከተለያዩ ተረፈ ምርቶችና ከቅጠላ ቅጠል ብስባሽ ኮምፖስት ማዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።
በላዕላይ ማይጨው ወረዳ የ"መዶገ" ገጠር ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ኪዳነ አበራ በበኩላቸው በ2017/18 የምርት ዘመን የተሻለ ምርት ለመሰብሰብ ማሳቸውን ደጋግመው ከማለስለስ ባለፈ ሁለት ኩንታል የተፈጥሮ ኮምፖስትን ጨምሮ 6 ኩንታል ዘመናዊ ማዳበሪያ ማዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
በመጀመሪያ ዙር በመስኖ ለምቶ የነበረውን የበቆሎ ምርት በመሰብሰብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸው ለመኸሩም የእርሻ ማሳቸውን ደጋግመው ማረሳቸውንና የዝናብ ውሃን እንዲያሰርግ በሚረዳ መልኩ ማሰናዳታቸውን ገልጸዋል።
በበጋ ወቅት የእርሻ መሬትን ደጋግሞ ማረስና ማለስለስ አረምን ከምንጩ ለማድረቅ እንደሚረዳ የገለጹት ደግሞ በወረዳው የመስኖና አዝርዕት ባለሙያ አቶ ብርሃነ ገብረመስቀል ናቸው።
የወረዳው አርሶ አደሮች ማሳቸውን መልሰው መላልሰው የማረስና የማለስለስ ስራ በወቅቱ መጀመራቸው የሚበረታታ ነው ያሉት ባለሙያው ወደ ሥራ ያልገቡ ካሉም ቶሎ እንዲገቡ አሳስበዋል።
በወረዳው የገጠር ልማት ጽህፈት ቤት በቁጠባ ዘርፍ የህብረት ስራና ገበያ አስተባባሪ አቶ ሹሻይ አሰፋ በበኩላቸው፣ ለ2017/18 የምርት ዘመን አርሶ አደሩ በአቅራቢያው ዘመናዊ ማዳበሪያ እንዲያገኝ በ15 የገጠር ቀበሌዎች የመጋዘንና የመሸጫ ማእከላት ተከፍተው አገልግሎት እየሰጡ ናቸው ብለዋል።
ለወረዳው 21 ሺህ 500 ኩንታል ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ በህብረት ስራ ዩኒየን በኩል መቅረቡንም ተናግረዋል።