አዲስ አበባ፤ መጋቢት 27/2017(ኢዜአ)፦ጥራት ያለው የፋይናንስና ኦዲት ሪፖርቶችን በማያቀርቡ የኦዲትና ሂሳብ ባለሙያዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ የኢትዮጵያ ሒሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ሒሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ ከተሰጡት ስልጣንና ተግባራት መካከል የሂሳብ ሙያ ማህበራት፣ በሒሳብና ኦዲት ሙያ ላይ በመሰማራት ለህዝብ የሂሳብ ሙያ አገልግሎት መስጠት የሚፈልጉ ባለሙያዎችን እና ድርጅቶችን መስፈርት በማውጣት ፍቃድ መስጠት መከታተልና መደገፍ ይገኙበታል።
በተጨማሪም ከተቋማት የሚመጡ የፋይናንስና ኦዲት ሪፖርቶች ደረጃቸውን ጠብቀው መከናወናቸውን የማረጋገጥና የመቆጣጠር ሥራዎችን ማከናወንም እንዲሁ።
የኢትዮጵያ ሒሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተር ፍቃዱ አጎናፍር ለኢዜአ እንዳሉት ቦርዱ የተለያዩ አለም አቀፍ ደረጃዎችን የመቀበልና የማስተዋወቅ ስራዎች እየሰራ ይገኛል።
ባለፉት ስምንት ወራት በአለም አቀፍ ደረጃ የወጡ ከዘላቂነትና አየር ንብረት ጋር የተያያዙ አዳዲስ ደረጃዎችን ለባንኮች፣ ለኢንሹራንሶች፣ የመንግስት የልማት ድርጅቶችና ለዘርፉ ሙያ ማህበራት ማስተዋወቅ መቻሉን ተናግረዋል።
የፋይናንስና የኦዲት ጥራት ግምገማ በማድረግ የተለያየ አይነት የፋይናንስና ኦዲት ሪፖርት ዝግጅትን ለማስቀረት እየሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።
ቦርዱ የባለሙያዎች ፍቃድ እድሳት እንደሚያደርግ ገልፀው፤ በተያዘው በጀት አመት እስካሁን ባለው ከ600 በላይ ባለሙያዎች ፍቃዳቸውን ማደሳቸውን ተናግረዋል።
እስካሁን ባለው በኦንላይን ሂደቱን አጠናቀው የእድሳት ምስክር ወረቀታቸውን ከቦርዱ ሲወስዱ መቆየታቸውን አንስተው ከቀጣይ አመት ጀምሮ የምስክር ወረቀቱንም ባሉበት ሆነው ማግኘት የሚችሉበት አሰራር እየተዘረጋ መሆኑን ጠቁመዋል።
ቦርዱ በኢትዮጵያ ጥራት ያለው የፋይናንስና ኦዲት ሪፖርት እንዲዘጋጅ ለማድረግ ሙያዊ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የባለሙያዎች ፍቃድ አሰጣጥ በቦርዱ በኩል መሰጠት ያለበት ቢሆንም እስካሁን ባለው በክልሎች ፍቃድ ሲሰጥ መቆየቱን ጠቅሰው ፤ ወጥነት ባለው መስፈርትና አሰራር ፍቃድ ለመስጠት የሚያስችል ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ወጥነት ያለው አሰራር መተግበር የታክስ ስወራና ሌሎች ማጭበርበሮችን ለማስቀረት የሚያስችልና የኦዲትና ፋይናንስ ጥራትን ለማስጠበቅ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸው፤ ጥራት ያለው ሪፖርቶችን በማያቀርቡ የኦዲትና ሂሳብ ባለሙያዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል።
ለቦርዱ የሚቀርበውን ሪፖርት ከወረቀት አሰራር ወደ ቴክኖሎጂ ለመቀየር ሶፍትዌር ማበልፀግ የሚያስችል ስራ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ለቦርዱ የሪፖርት ጥራት ግምገማ በማድረግ የተለያዩ ማስተካከያ እንዲያደርጉ ለተቋማት ግብረ መልስ እንደሚሰጥ አንስተው በቀጣይ ግን ከማስተማር ባለፈ የተጠያቂነት አሰራርን የማስፈን ስራ ይሰራል ብለዋል።