አዲስ አበባ፤ መጋቢት 29/2017(ኢዜአ)፦ የአደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድ አደጋን በራስ አቅም ምላሽ የመስጠት አቅምን በማጎልበት የሀገርን ሉዓላዊነትና ክብር ለማስጠበቅ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር) ገለጹ፡፡
6ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጋቢት 9 ቀን 2017 ዓ.ም ባካሄደው 20ኛ መደበኛ ስብሰባ የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ እንዲያቀርብ ለዝርዝር እይታ ለውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መመራቱ ይታወሳል።
ቋሚ ኮሚቴው ዛሬ በረቂቅ አዋጁ ላይ የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ አካሂዷል።
በመድረኩ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ የአዋጁ መውጣት በኢትዮጵያ የሚከሰቱ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን በራስ አቅም ምላሽ በመስጠት ብሔራዊ ደህንነትና ክብርን ለማስጠበቅ ያግዛል ብለዋል።
በተጨማሪም አደጋን ለመከላከል፣ ዝግጁነትን ለማረጋገጥና ወቅታዊ ምላሾችን መስጠት በማስቻል የአደጋ ስጋት አመራር ውጤታማ እንዲሆን እንደሚያደርግም ገልጸዋል።
በዚሁ መሰረት በቅድመ አደጋ፣ በአደጋ እና ድህረ አደጋ ለሚወሰዱ የአደጋ ስጋት ቅነሳ ምላሽና መልሶ ማቋቋም የሚሆን የአደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድ እንደሚቋቋም ተናግረዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች በአዋጁ የተቋማትን ቅንጅት ለማረጋገጥ የተነሱ ሃሳቦች መልካም መሆናቸውን ገልጸዋል።
አዋጁ በመሰረታዊነት አሰራር ላይ በማተኮር ግቡን ሊያሣካ እንደሚገባም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር) በሰጡት ምላሽ እና ማብራሪያ፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ማህበራዊ ኃላፊነትን የሚያረጋግጡ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል ነው ያሉት፡፡
የአደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድ ዘላቂነት ባለው መልኩ ህብረተሰቡን በማሳተፍ ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የአደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድ ለሚከሰቱ አደጋዎች በራስ አቅም ምላሾችን ለመስጠትና የሀገርን ሉዓላዊነትና ክብር ለማስጠበቅ ጉልህ ፋይዳ ያለው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈትሂ ማህዲ(ዶ/ር)፤ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ሲታወጅ ታሪክ ቀያሪ ብሎም የቀደሙ ስብራቶችን የሚጠግን እንደሚሆን ገልጸዋል።
እንደ ሀገር ከዚህ ቀደም የነበሩ የመደጋገፍና የመረዳዳት ባህልን በተደራጀ አግባብ መምራት የሚያስችል መሆኑንም ጠቁመዋል።