የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ
ልዩ ዘገባ

በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የዘርፉ ሙያተኞች ተቀራርበው መስራት አለባቸው

Apr 8, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 29/2017(ኢዜአ)፦ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት የዘርፉ ሙያተኞች ተቀራርበው መስራት እንዳለባቸው ተገለፀ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማና መሰረተ ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ አሰላሳይ ግሩፕ(think tank) ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብ ላይ ከዘርፉ ተዋናዮች ጋር ምክክር አካሂዷል።


በመድረኩ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ አሰላሳይ ግሩፕ(think tank) ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብ መዘጋጀት ፋይዳን የሚዳስስ ጽሁፍ ቀርቦ አስተያየት ተሰጥቶበታል።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ የትምጌታ አስራት በዚህ ወቅት የኢትዮጵያን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ያሉበትን ዘርፈ ብዙ ማነቆዎችን በመፍታት ወደ ላቀ የእድገት ደረጃ ማሸጋገር ይገባል ብለዋል።

ዘርፉ ዘመኑን በሚዋጅ መልኩ ውጤታማ እንዲሆን ከኮንስትራክሽን ጋር በተያያዘ በተለያዩ መስኮች ያሉ ሙያተኞችን በማቀናጀት አቅማቸውን ማሳደግ የሚችሉበትን ሁኔታ ማጠናከር ያስፈልጋል ነው ያሉት።

መንግስትም የኮንስትራክሽን ዘርፉን ለማሳደግ የዘርፉን ሙያተኞች በማቀራረብ ለሀገር የሚጠቅሙ ሀሳቦችን በጋራ ለማፍለቅ ዝግጁ መሆኑን አብራርተዋል።

በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት የዘርፉ ሙያተኞች ከምንጊዜውም በላይ ተቀራርበው በመስራት አስተዋጿቸውን እንዲያጠናክሩም ጠይቀዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ እሸቱ ተመስገን(ዶ/ር) በበኩላቸው ረቂቅ ደንቡ ከዲዛይንና ከኮንስትራክሽን ህግ ጋር ተያይዞ በቂ እውቀትና ልምድ ባካበቱ ሙያተኞች መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

ረቂቅ ደንቡ በኮንስትራክሽን ዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮች ላይ ተገቢውን ጥናትና ምርምር በማድረግ መፍትሄ የሚሹ ጉዳዮችን በመለየት የህግ ማዕቀፍ እንዲዘጋጅላቸው ጭምር አቅም የሚፈጥር በመሆኑ ደንቡ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በመድረኩም ከባለድርሻ አካላት አስተያየት በማሰባሰብ ለረቂቁ ግብዓት እንዲሆን ለከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር መሰጠቱን አንስተዋል።

በተጨማሪም ሚኒስቴሩ በዘርፉ የሚሰራቸው ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ሙያዊ እገዛ ለማድረግ እንደሚረዳ ተናግረዋል።

በውይይት መድረኩ የተሳተፉ የዘርፉ ተዋናዮች በበኩላቸው ለዘርፉ እድገት አሰላሳይ ግሩፕ ለማቋቋም ረቂቅ ደንቡ መዘጋጀቱ ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.