አርባ ምንጭ፤ መጋቢት 30/2017 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ምርቶቻቸውን ከማስተዋወቅ ባለፈ የገበያ ትስስር በመፍጠርና ተኪ ምርቶችን በማምረት ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች ገለጹ።
በአርባ ምንጭ ከተማ በተካሄደው ክልል-አቀፍ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ፣ ኤግዚቢሽንና ባዛር ላይ የተሳተፉ አምራች ኢንዱስትሪዎች እንደገለጹት፣ ንቅናቄው ከተጀመረ ወዲህ የዘርፉ ችግር በመሠረታዊነት እየተፈታ ነው።
አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል የዊን ውሃ ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ አቶ ወገኔ ዳና የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተኪ ምርቶችን በጥራትና በስፋት በማምረት ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል።
በወላይታ ዞን ቦዲቲ ከተማ በሚገኘው የውሃ ማምረቻ ፋብሪካ ከ100 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ጠቅሰው፣ ንቅናቄው የገበያ ትስስር ከመፍጠር ባለፈ ለውሃ መያዣ የሚያስፈልገውን እቃ በራስ አቅም ለማምረት እንዳነሳሳቸው ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም የማሽን ተከላ ሥራ ላይ መሆናቸውን ነው ያስታወቁት
በእጅ ጥበብ የሚሠሩ ሸሚዝ፣ ፎጣ፣ ቀሚስ፣ ቲሸርት፣ ኮፍያና መሰል አልባሳትን በማምረት ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገራት ገበያ እያቀረቡ መሆኑን የተናገረው ደግሞ በአርባ ምንጭ ከተማ የሚገኘው ቤሬ የሐር ልማት ድርጅት የምርት ክፍል ሃላፊ ወጣት ዳዊት ደሌ ነው።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ምርቶቻቸውን በማስተዋወቅ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የገበያ ትስስር እንደፈጠረላቸው ተናግሯል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኢንዱስትሪ ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ቦጋለ ቦሼ በበኩላቸው እንዳሉት፣ በክልሉ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረ ወዲህ የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ እየተነቃቃ መጥቷል።
ንቅናቄውን ተከትሎ በተኪና ወጪ ምርቶች ላይ የባለሀብቶችን ተሳትፎ ከማሳደግ ባለፈ በገበያ ላይ ተወዳዳሪና ጥራት ያለው ምርት እንዲያመርቱ እያገዘ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
አምራች ኢንዱስትሪው ከግብአት አቅርቦት፣ ከገበያ ትስስርና ምርታማነትን ከማሻሻልና ከማሳደግ አንጻር ያለበት ችግር እንዲፈታም ቢሮው ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ዶክተር ቦጋለ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት በሚል መሪ ሃሳብ በአርባ ምንጭ ከተማ ለሦስት ቀናት ሲካሄድ የነበረው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ፣ ኤግዚቢሽን እና ባዛር ተጠናቋል።