ሮቤ፤ሚያዝያ 2/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮ ቴሌኮም በሮቤና አሰላ ከተሞች የአምስተኛውን ትውልድ የሞባይል ኔትወርክ አገልግሎት ዛሬ አስጀመረ።
ኩባኒያው ለህዝብ የሚሰጠውን አገልግሎት ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ የደቡብ ምሥራቅ ሪጅን ጽህፈት ቤቱን በባሌ ሮቤ በአዲስ መልክ ሥራ ማስጀመሩ ተመልክቷል።
በማስጀመሪያ መርሀ ግብሩ ላይ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩና የኩባንያው ከፍተኛ አመራር አባላት እንዲሁም የሮቤ ከተማና የባሌ ዞን አመራሮችና የአገልግሎቱ ደንበኞች ተገኝተዋል።
ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ፍሬህይወት ታምሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ኩባኒያው አገልግሎት አሰጣጡን በማሻሻል ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን የማድረግ ጉዞ ላይ ይገኛል።
የአምስተኛው ትውልድ ኔትወርክ አገልግሎት የዓለማችን ፈጣንና ቀልጣፋ የኔትወርክ አገልግሎት መሆኑን አንስተው ዛሬ አገልግሎት የጀመሩትን ጨምሮ በኢትዮጵያ በ16 ከተሞች አገልግሎቱን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
የአምስተኛው ትውልድ (5ጂ) የሞባይል ኔትወርክ አገልግሎት ደንበኞች ዘመኑን የሚመጥን ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
ዛሬ በሮቤና አሰላ ከተሞች የተጀመረው የአምስተኛው ትውልድ የሞባይል ኔትወርክ አገልግሎት በከተሞቹና በአካባቢው የሚከናወኑ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስራዎችን በተሻለ ደረጃ ለማከናወን የሚያግዝ ነውም ብለዋል።
ኩባኒያው ለህዝብ የሚሰጠውን አገልግሎት ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግና ለማዘመን የደቡብ ደቡብ ምሥራቅ ሪጅን ጽህፈት ቤቱን በባሌ ሮቤ በአዲስ መልክ ሥራ ማስጀመሩንም አክለዋል።
የሪጅኑ መከፈት የተቀናጀ የቴሌኮምና የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን መሰረተ ልማትን ለማህበረሰቡ ለማቅረብ እየተደረገ የሚገኘውን ጥረት በተሻለ ሁኔታ እንደሚያግዝም አመልክተዋል።
በኢትዮ ቴሌኮም የደቡብ ደቡብ ምሥራቅ ሪጅን ጽህፈት ቤት የሁለቱን የባሌ ዞኖችና ከፊል አርሲ ዞኖችን እንደሚያካቲት ከኩባኒያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
#Ethiopian_News_Agency
#ኢዜአ
#Ethiopia