አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 2/2017(ኢዜአ):- እንግሊዝ የጉምሩክ ኮሚሽን አሰራር ማዘመንን ጨምሮ ሌሎች የሪፎርም ስራዎችን እንደምትደግፍ በኢትዮጵያ የእንግሊዝ ኤምባሲ ምክትል ሚሲዮን መሪ ሉክ ቡሎክ ገለጹ።
የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ በኢትዮጵያ የእንግሊዝ ኤምባሲ ምክትል ሚሲዮን መሪ ሉክ ቡሎክን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
ኮሚሽነር ደበሌ ተቋሙ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተከናወኑ የለውጥ ስራዎችን አስመልክቶ ለአምባሳደሩ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን በጋራ ለመስራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይም መክረዋል።
በውይይቱ ላይ በእንግሊዝ የጉምሩክ አገልግሎትና በኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስና በዘርፉ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት በትብብር ለመስራት ፍላጎት እንዳለ ኮሚሽነር ደበሌ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የእንግሊዝ ኤምባሲ ምክትል ሚሲዮን መሪ ሉክ ቡሎክ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት እየሰጠ ያለበትን ሂደት አድንቀዋል።
እንግሊዝ በኮሚሽኑ እየተከናወኑ የሚገኙ የለውጥ ስራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ ድጋፍ እንደምታደርግ መግለጻቸውንም የኮሚሽኑ መረጃ ያመለክታል።