የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

የግብርና ዘርፉ ለአጠቃላይ ሀገራዊ እድገት ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል - ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር)

Apr 14, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 5/2017(ኢዜአ)፦ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የግብርናው ዘርፍ ለአጠቃላይ ሀገራዊ እድገት ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) ገለጹ።

የ2017 በጀት ዓመት የሦስተኛው ሩብ ዓመት የ100 ቀን አፈጻጸም እና የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራ አፈጻጸም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት ተገምግሟል።

የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) የዘርፎች አፈጻጸምን አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም በግብርና ዘርፍ ዘንድሮ ከታቀደው 8 ነጥብ 4 በመቶ አጠቃላይ እድገት ውስጥ 6 ነጥብ 1 በመቶ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ግብ መጣሉን ገልጸዋል።

ለዚህም በመኸር፣ በበልግ እና መስኖ መሰራት ያለባቸው ስራዎች ታቅደው ወደ ስራ መገባቱን አብራርተዋል።

ባለፈው የመኸር ወቅት 20 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን እና ይህም ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ3 ሚሊዮን ሄክታር ብልጫ እንዳለው ጠቅሰዋል።

ይህም በስንዴ ምርት ብቻ ሲታይ ዘንድሮ 152 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መመረቱን ገልጸው፤ የግብርና ዘርፉ ለአጠቃላይ ሀገራዊ እድገት ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አመላክተዋል።

በሰብል ምርት የተያዘው ግብም ሙሉ በሙሉ ማሳካቱን ጠቁመዋል።

በእንስሳት ሀብት ልማትም በተለይ በሌማት ትሩፋት የተከናወነው ስራ ከፍተኛ ውጤት እንደተገኘበት አብራርተዋል።

በወተት፣ በእንቁላል፣ በዶሮ፣ በማር እና በአሳ ምርት እንዲሁ ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን ገልጸው፤ የተመዘገበው ውጤትም በሀገራዊ ምርት እድገቱ ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የግብርናው ዘርፍ ገበያን ከማረጋጋት እንዲሁም የኑሮ ውድነትን ከመቅረፍ አንጻር ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት የግብርናው ዘርፍ 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ለኤክስፖርት አስታወጽኦ ማበርከቱን አንስተው አፈጻጸሙ ከእቅዱ የ19 በመቶ ብልጫ እንዳለውም ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.