የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው እየተመዘገበ ያለው ስኬት ተጠናክሮ ይቀጥላል - ሚኒስትር አህመድ ሽዴ

Apr 14, 2025

IDOPRESS

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 5/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው እየተመዘገበ ያለው ስኬት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ገለጹ።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት የመንግስት የልማት ድርጅቶች አፈጻጸም በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉንም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

የ2017 በጀት ዓመት የሦስተኛው ሩብ ዓመት የ100 ቀን አፈጻጸምና የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራ ያለፉት ዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት ተገምግሟል።ፀ

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ የማክሮ ኢኮኖሚና የዘርፎች አፈጻጸም አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም የዘንድሮው አመት የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የተደረገበት በመሆኑ ከሌሎቹ አመታት ለየት ያለ መሆኑን ገልጸዋል።

በታሪክም ትልቁ የኢኮኖሚ ሪፎርም የተካሄደበት መሆኑን ጠቅሰው፤ የፊስካል ፖሊሲዎች ተግባራዊ መደረጋቸውንም ተናግረዋል።

እንዲሁም የእድገት አማራጮችን በማስፋት የግሉን ሴክተር ሚና ማሳደግ የሚያስችሉ የሪፎርም ስራዎች የተከናወኑበት መሆኑን ጠቁመዋል።

ከእድገት አፈጻጸም አንጻርም ያለፉት ዘጠኝ ወራት ጠንካራ ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን ጠቅሰዋል።

የዋጋ ንረትን በመቆጣጠር ረገድ ጥሩ ውጤት መመዝገቡን እና ካለፉት ወራት የቀነሰበት ሁኔታ መኖሩን ተናግረዋል።

በአጠቃላይ የገቢ አቅምን ለማሳደግ የተሰራው ስራ ውጤታማ መሆኑን ገልጸው፤ ከዚህ በላይ አጠናከሮ መቀጠል እንደሚገባ በመድረኩ መነሳቱን አስታውቀዋል።

ሚኒስትሩ አክለውም ባለፉት ዘጠኝ ወራት የመንግስት የልማት ድርጅቶች አፈጻጸም በከፍተኛ ሁኔታ እድገት አስመዝግቧል ብለዋል።

በኤክስፖርት ረገድም መልካም አፈጻጸም መገኘቱን ጠቅሰው፤ አጠቃላይ የውጭ ምንዛሪ ክምችትና የባንኮች የምንዛሪ ግኝት መሻሻሉን ገልጸዋል።

የታክስ አስተዳደርን በማሻሻል እንዲሁም የታክስ ህግ ተገዥነትን በማሳደግ ረገድ የተከናወነው ስራ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቡን አስታውቀዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻያው ሪፎርሙን ተከትሎ የሚመጣውን ጫና ለማስቀረት ከፍተኛ የበጀት ድጎማ መደረጉን ተናግረዋል።

ለአብነትም ለማዳበሪያ፣ ለነዳጅ፣ ለምግብ ዘይት፣ መድሀኒት እንዲሁም የመንግስት ሰራተኞች ደሞዝ ጭማሪ መደረጉን አንስተዋል።

የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በሴክተሮች አፈጻጸም እና በኢኮኖሚ እድገት በመልካም የአፈጻጸም ደረጃ ላይ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.