መቀሌ፤ሚያዝያ 6/2017(ኢዜአ)፡-በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተደደር የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ የተዘጋጀው የግብርና ስትራቴጂክ እቅድ ውሃና የአካባቢን ጸጋ ማዕከል ያደረገ ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ እንደሚያስችል ተገለጸ።
በአዲሱ የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ ላይ በመመስረት ቢሮው ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የግብርና ስትራቴጂክ እቅድ ላይ ዛሬ በመቀሌ ከተማ ውይይት ተካሄዷል።
በውይይት መድረኩ የክልሉ ጊዜያዊ አስተደደር የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ሀላፊ እያሱ አብረሃ(ዶ/ር ) እንዳሉት፥ የተዘጋጀው የግብርናና የተፈጥሮ ሀብት ስትራቴጂክ እቅድ የክልሉን የግብርና ምርት በዓይነትና ጥራት ተወዳዳሪነትን የሚያሳድግ ነው።
አዲሱ የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ የሪፎርም ስራዎችን የሚያጠናክር፤ምርጥ ተሞክሮዎችን የሚያስፋፋ፣ውሃና የአካባቢን ጸጋ ማዕከል ያደረገ ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ እንደሚያስችል ገልጸዋል።
ፖሊሲውን ማዕከል በማድረግ በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የተሰናዳው የግብርና ስትራቴጂክ ትግበራ እቅድ የክልሉን የመሬት አቀማመጥ፣የውሃና ተፈጥሮ ሃብት ጸጋዎች ላይ በመመስረት መሆኑን ተናግረዋል።
በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችል መሆኑም ጠቅሰዋል።
እቅዱ በሚቀጥሉት 20 ዓመታት በግብርናው ዘርፍ መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጣ መሆኑን የገለጹት እያሱ አብረሀ (ዶ/ር )፥የመስኖና የእንስሳት ሃብት ልማት በእጥፍ የሚያሳድግ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዚህም የገጠሩን ማህበረሰብ አኗኗር ዘይቤን በዘላቂነት የሚያሻሽል መሆኑንም አክለዋል።
በቀጣይ የመኸር ወቅት ተግባራዊ መደረግ እንደሚጀመር ጠቁመው፤ በተለይ በዘርፉ ባለሃብቶችን በማሳተፍና ድጋፍ በማድረግ ሴቶችና ወጣቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ትኩረት መደረጉን አንስተዋል።
የግብርና ስትራቴጂክ ተግበራ እቅድ ካዘጋጁት የባልድርሻ አካል አባላት መካከል የዓይንሸት ተስፋይ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥እቅዱ በተፈጥሮና እንስሳት ሃብት ዙሪያ ሰፊ የስራ እድል የሚፈጥር እና በግብርና ዘርፍ የወጣቶች ተጠቃሚነትን ከፍ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
እቅዱ የውስጥ ኢኮኖሚ አቅምን በማሳደግ የውሃ እና መሬት ብክነትን በመቀነስ በተለይ ትኩረት ያልተሰጠውን የክልሉ ተዳፋት ቦታዎች ለማልማትና የኢኮኖሚ እድገትን ለማፋጥን ትልቅ አቅጣጫ የያዘ መሆኑን የገለፁት ደግሞ ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ ገብረመድህን ወልደዋህድ (ዶ/ር ) ናቸው፡፡
እርሻ መሰረተ ልማትን በማስፋፋት የግል ባለሃብቱን ተሳትፎ የሚያበረታታ እና እርዳታ በማስቀረት ዘላቂ ልማት የሚያመጣ ስትራቴጂክ እቅድ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡