የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

በክልሉ 98 ሺህ ቶን የሚጠጋ የድንጋይ ከሰል ለማዕከላዊ ገበያ ቀርቧል

Apr 15, 2025

IDOPRESS

ቦንጋ፣ ሚያዚያ 6/2017 (ኢዜአ)፡-በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በበጀት ዓመቱ ያለፉት ዘጠኝ ወራት 98 ሺህ ቶን የሚጠጋ የድንጋይ ከሰል ምርት ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን የክልሉ ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ኤጀንሲ አስታወቀ።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ገብረማርያም ሰጠኝ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከውጭ ከምታስገባቸው ምርቶች መካከል የድንጋይ ከሰል አንዱ ሲሆን በክልሉም በሰፊው ይገኛል።

ቀደም ሲል ሀብቱ ተገቢውን ትኩረት ተነፍጎት በመቆየቱ ለአካባቢውና ለሀገር ኢኮኖሚ የሚጠበቅበትን አስተዋጾ ሳያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ይሁንና ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከዘርፉ የሚፈለገውን ጥቅም ለማግኘት በተወሰዱ እርምጃዎችና ወደምርት ሥራ በመገባቱ የድንጋይ ከሰሉን ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ መቻሉን ተናግረዋል።

በዚህም በተያዘው በጀት ዓመት 200 ሺህ ቶን የድንጋይ ከሰል ለማዕከላዊ ከበያ ለማቅረብ ታቅዶ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ 98 ሺህ ቶን የሚጠጋ የድንጋይ ከሰል ለማቅረብ ተችሏል ብለዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ በዘርፉ ለመሰማራት ፍቃድ ከወሰዱ ከ20 በላይ ማህበራት መካከል በአሁኑ ወቅት ወደምርት የገቡት ስምንት ብቻ ናቸው።

ይህም ዕቅዱ እንዳይሳካ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፣ በቀጣይ ዕቅዱን ለማሳካት ወደስራ ያልገቡትንና ፍቃድ ለመውሰድ በሂደት ላይ ያሉ ማህበራትን ወደ ስራ ለማስገባት ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ብለዋል።

የድንጋይ ከሰል ምርትን ጨምሮ ከማዕድን ዘርፍ በበጀት ዓመቱ ለሰባት ሺህ 717 ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ወደ 6 ሺህ የሚጠጉትን ተጠቃሚ ለማድረግ መቻሉንም አስታውቀዋል።

ዘርፉን ለማነቃቃት የተወሰደው እርምጃ ለዘመናት በሀብቱ ሳይጠቀም የቆየው የአካባቢው ነዋሪ ተጠቃሚ እንዲሆን እድል መፍጠሩን የገለጹት ድግሞ በክልሉ የዳውሮ ዞን ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ሀላፊ አቶ ሀይሌ ዱባለ ናቸው።


በተለይም በዞኑ የተቋቋመው የድንጋይ ከሰል ማበልፀጊያ ፋብሪካ ለበርካቶች የሥራ ዕድል መፍጠሩንና ለአካባቢው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ከፍተኛ መነቃቃት መፍጠሩንም ተናግረዋል ።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ግምገማ መድረክ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በቦንጋ ከተማ መካሄዱ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.