ሆሳዕና፣ ሚያዚያ 10/2017 (ኢዜአ)፡-በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለትንሳኤ በዓል የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት ግብረ ኃይል ተቋቁሙ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡
የቢሮው ኃላፊ አቶ ዳንኤል ዳምጠው ለኢዜአ እንደገለጹት ለትንሳኤ በዓል የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰትና ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ግብረሀይል ተቋቁሞ በቅንጅት እየተሰራ ነው።
የእንስሳት ተዋጽኦ፣ የአትክልትና የፋብሪካ ምርቶች ከአምራቹ ለሸማቹ በቀጥታ የሚደርስበት አሰራር መዘርጋቱን ገልጸው፣ ከሰንበት እስከ ሰንበት ገበያዎች ምርቶቹ በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ መቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡
በዚህም በክልሉ ለዞንና ለልዩ ወረዳዎች ከ224 ሺህ 300 በላይ ሊትር የምግብ ዘይት ለዞንና ለልዩ ወረዳዎች መሰራጨቱን አቶ ዳንኤል ገልጸዋል።
በገበያው የምርት እጥረትና ያልተገባ የዋጋ ጭማሪን ለመከላከልም ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ህብረተሰቡም ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ፣ ምርት ደብቀው የሚያከማቹና በምግብ ምርት ላይ ባዕድ ነገር ቀላቅለው የሚሸጡ ስግብግብ ነጋዴዎች ሲገጥሙት ለሚመለከተው የመንግስት አካል ፈጥኖ ጥቆማ በመስጠት የተለመደ ትብብሩን እንዲያጠናክርም ጠይቀዋል።
በሆሳዕና ከተማ የአራዳ ቀበሌ ነዋሪ አቶ መኮንን ሻንቆ በሰጡት አስተያየት፣ በከተማው የበዓል ገበያው በአቅርቦትም ሆነ በዋጋ የተሻለ መሆኑን አንስተዋል።
በበዓል ገበያ የምርት የአቅርቦት እጥረት እንዳያጋጥም አስተዳደሩ እያደረገ ያለው የቁጥጥር ሥራ ሸማቹን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በከተማው የሄጦ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ሊንረንሴ ዮሐንስ በበኩላቸው በከተማው በዋናው ገበያም ሆነ በሰንበት ገበያዎች ሁሉም የምርት ዓይነት መቅረቡንና እጥረት እንደሌለ ጠቁመው፣ "በገበያው እንደፍላጎታችን እየሸመትን ነው" ብለዋል።
ሽንኩርትን ጨምሮ ሌሎች ለበዓል የሚያስፈልጉ ምርቶች ላይ ከወትሮው የዋጋ ጭማሪ አለመኖሩ ገበያውን የተረጋጋ ማድረጉን ጠቅሰው፣ በገበያው ክትትልና ቁጥጥር መደረጉ ውጤት አምጥቷል፤ በቀጣይም ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።