ደሴ፤ ሚያዚያ 14/2017 (ኢዜአ)፡-በደሴ ከተማ አስተዳደር ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የመንገድ ግንባታ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
የባለሰልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አንዷለም እሸቱ ለኢዜአ እንደገለጹት በከተማው የመንገድ ተደራሽነትን በማስፋት የከተማውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ለማቀላጠፍ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።
በዚህም በዘንድሮው ዓመት ብቻ የኮሪደር ልማቱን ጨምሮ አራት ኪሎ ሜትር የመንገድ ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።
ከግንባታዎቹ መካከል ከመነሃሪያ አረብ ገንዳ መስጅድ አካባቢ የአንድ ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥና ከገብርኤል-ባህር ሺሽ-ቁርቁር አንድ ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ሥራዎች ይገኙበታል።
በተጨማሪም ከቧንቧ ውሃ-ሮቢት-ወሎ ባህል አምባ እየተገነባ የሚገኘው ሁለት ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ሥራ እንደሚገኝበት ገልጸዋል።
ለመንገዶቹ ግንባታ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት መመደቡን ጠቁመው ሁሉም መንገዶች በተያዘው በጀት ዓመት መጨረሻ እንደሚጠናቀቁ አስታውቀዋል።
ለመንገዶቹ ግንባታም መንግስት ከመደበው በጀት በተጨማሪ ህብረተሰቡ በገንዘብ፣ በቁሳቁስና በጉልበቱ የራሱን አስተዋጾ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የደሴ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ሉባባ በሽር በበኩላቸው በከተማው ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተለያዩ መሰረተ ልማቶች እየተፋጠኑ በመሆኑ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የመንገዶቹ ግንባታ የህብረተሰቡን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ የሚመልሱ በመሆናቸው በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ በጥራት እንዲጠናቀቁ ነዋሪውም የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።
በከተማው ግንባታቸው በመከናወን ላይ ያሉ የአስፋልት መንገዶች የከተማውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንደሚያነቃቁ የገለጹት ደግሞ ሌላዋ የደሴ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አባይነሽ ሀይሉ ናቸው፡፡