አዲስ አበባ፤ሚያዚያ 14/2017(ኢዜአ)፦በዘንድሮ የበጋ መስኖ ስንዴ ከለማው ሰብል እስካሁን ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ የደረሰ ምርት መሰብሰቡን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሌላ በኩል በበልግ ወቅት 98 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማምረት እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል።
በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ኢሳያስ ለማ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አርሶ አደሮች በመኸር፣ በበልግና በበጋ መስኖ ዓመቱን ሙሉ እንዲያመርቱ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ሳይታረሱ የቆዩ መሬቶችን ወደ ልማት በማስገባት በዘር የሚሸፈን የመሬት መጠንን መጨመር፣የግብርና ቴክኖሎጂ፣ግብዓትና ምርጥ ዘሮችን መጠቀም ለምርትና ምርታማነት መጨመር ምክንያት መሆናችውን አመላክተዋል፡፡
በበጋ መስኖ ልማት የተጀመሩ ሥራዎችም አርሶ አደሩ በዓመት በሶስት ዙር እንዲያመርት በማድረግ ከፍተኛ ምርት እያስገኙ ናቸው ብለዋል።
በዚህ ዓመት ከበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 172 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማምረት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን ጠቅሰዋል።
እስካሁን ሶስት ነጥብ አምስት ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን የገለጹት አቶ ኢሳያስ፥ ቀደም ብሎ የተዘራ እና የደረሰ የበጋ መስኖ ስንዴ ምርት እየተሰበሰበ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።
በዚህም እስካሁን በ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ የደረሰ ምርት መሰብሰቡን ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ወቅቱ የበልግ ሰብል ልማት የሚከናወንበት መሆኑን ጠቅሰው፥ በበልግ አብቃይ አካባቢዎች በስፋት ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል፡፡
በዚህም በዘንድሮ በልግ ሶስት ነጥብ ሰባት ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን 98 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማምረት መታቀዱን ጠቅሰው፥ እስካሁን 2 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ገልጸዋል፡፡
አርሶ አደሮች በቀሪ የበልግ ወቅት በዘር ያልተሸፈነ መሬታቸውን በመሸፈን ቀድሞ በዘር የተሸፈነውን የአረም ቁጥጥርና ተባይ ክትትል እንዲያደርጉም አስገንዝበዋል፡፡