የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

ክልሉ የሚያመነጨውን ገቢ በተገቢው በመሰብሰብ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በጥራት ለማጠናቀቅ ርብርብ ይደረጋል-አቶ ኦርዲን በድሪ

Apr 23, 2025

IDOPRESS

ሐረር፣ሚያዝያ 14/2017(ኢዜአ)፦የሐረሪ ክልል የሚያመነጨውን ገቢ በተገቢው በመሰብሰብ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜና በጥራት ለማጠናቀቅ የተቀናጀ ርብርብ እንደሚደረግ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ተናገሩ።


የሐረሪ ክልል የአስፈፃሚውን እና የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ተቋማትን የዘጠኝ ወራት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ዛሬ ገምግሟል።


በስራ አፈፃፀሙ ግምገማም የክልሉ የካፒታል ፕሮጀክቶች አፈፃፀም እና በክልሉ ገቢ አሰባሰብ ረገድ የተከናወኑ ተግባራት ተገምግመዋል።


በመድረኩ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተደድር ኦርዲን በድሪ እንዳሉት፥ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የክልሉን ህዝብ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በተገቢው መንገድ ለመመለስ አበረታች ስራዎች ተሰርተዋል።


የክልሉ ኢኮኖሚ የሚያመነጨውን ያህል ገቢ በተገቢው በመሰብሰብ በመተግበር ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜና በጥራት እንዲጠናቀቁ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።


በዚህ ረገድ ኃላፊነታቸውን በተገቢ ሁኔታ የማይወጡ አመራሮችና ተቋማት ላይ የተጠያቂነት አሰራር እንደተዘረጋና አስፈላጊው እርምጃ እንደሚወሰድም አቶ ኦርዲን ገልፀዋል።


የክልሉ ኢንተርፕራይዞች ልማትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማኢል ዩሱፍ፤ በክልሉ ባለፈው በጀት ዓመት የካፒታል ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ለአገልግሎት በማብቃት ረገድ አበረታች ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።


በቀሪ ጊዜያትም ፕሮጀክቶችን በተቀናጀ መንገድ ዳር በማድረስ የህዝብን የልማት ጥያቄዎች በላቀ ደረጃ መመለስ ይገባናል ብለዋል።


የክልሉ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብይ አበበ በበኩላቸው፥ ፕሮጀክቶችን በተጠያቂነት መንፈስ በጊዜ ማጠናቀቅ እንደሚገባ ገልፀው፥ ክልሉ የሚያመነጨውን ያህል ገቢ አሟጦ የመሰብሰብ ሂደትን ማጠናከር እንደሚገባም ገልፀዋል።


ተሳታፊዎች በበኩላቸው፥ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ለሚያጠናቅቁ ተቋማት ዕውቅና ከመስጠት ጎን ለጎን የተሰጣቸውን ተልዕኮ በአግባቡ በማይወጡት ላይ የተጠያቂነት አሰራር ተግባራዊ ሊደረግ ይገባል ብለዋል።


ዛሬ የተጀመረው የክልሉ የዘጠኝ ወራት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ግምገማ የተለያዩ ሴክተሮችን የስራ አፈፃፀም የገመገመ ሲሆን ሂደቱ እስከ ነገ እንደሚቀጥልም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.