አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 14/2017 (ኢዜአ)፡- ቦይንግ የአፍሪካ ቢሮውን በአዲስ አበባ ከፍቷል።
ቦይንግ የአፍሪካ ቢሮውን በአዲስ አበባ መክፈቱ ዓለማቀፋዊ ራዕያችንን ለማሳካት ወሳኝ እርምጃ ነው ሲሉ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትሩ በቢሮው መክፈቻ ስነስርዓት ላይ ተገኝተው ባደረጉትር ንግግር የቢሮው መከፈት በዓለም አቀፉ አቪዬሽን የኢትዮጵያን እድገት ማሳያ ከመሆን ባሻገር የተሳሰረችና የበለፀገች አፍሪካን እውን የማድረግ አለም አቀፋዊ ራዕይን ለማሳካት የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ እያደገ የመጣ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ አቅም መፍጠሯን የጠቆሙት ሚኒስትሩ በብሔራዊ ትራንስፖርት ካውንስል የሚመራ የዘርፉን መሠረተ-ልማት ለማዘመን፣ የትራንስፖርት ንግድ ወጪን ለመቀነስ እና አፍሪካን ለማስተሳሰር የሚያስችል የአስርት አመታት ፍኖተ ካርታ አዘጋጅተን እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
ቦይንግ ቢሮውን በአዲስ አበባ በከፈተበት ሥነ-ስርዓት ላይ የቦይንግ የመካከለኛው ምስራቅ፣ ቱርክ፣ አፍሪካ እና ማዕከላዊ ኤዥያ ፕሬዝዳንት ሚስተር ኩልጅት ጋታ፣ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ፣ የኢትጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግስቴ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰውና ሌሎችም የኩባንያው አመራሮች መገኘታቸውን ከትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡