ሐረር፤ ሚያዚያ 15/2017(ኢዜአ)፦ በሐረሪ ክልል ዘላቂ ሰላምና የህግ የበላይነትን በማጠናከር የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች በተቀናጀ መንገድ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ርዕሰ መስተደድር ኦርዲን በድሪ አስታወቁ።
ለሁለት ቀናት የተካሄደው የክልሉ የ2017 በጀት አመት የዘጠኝ ወራት የስራ አፈፃፀም ግምገማ ማምሻውን ተጠናቋል።
አቶ ኦርዲን በድሪ በወቅቱ እንደገለጹት በክልሉ በዘንድሮ በጀት አመት ዘጠኝ ወራት የገጠርና የከተማውን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት ያረጋገጡ አበረታች ልማቶች ተከናውነዋል።
በሌሎችም በማህበራዊ፣ በምጣኔ ሃብት እንዲሁም በሰላምና መልካም አስተዳደር ዘርፎች የህዝቡን መሠረታዊ ጥያቄዎች የመለሱ ተግባራት መከናወናቸውን አመልክተዋል።
በቀጣይም የተገኙ ውጤቶችን በማስፋት ብዙ መትጋትና መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
በተለይም ዘላቂ ሰላምና የህግ የበላይነትን በማጠናከር የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በፍትህና በፀጥታ ተቋማት የተጀመሩ አበረታች የሪፎርም ስራዎች በተቀናጀ መንገድ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
ሴክተሮች የተቀናጀና የተናበበ ስራዎችን በላቀ ደረጃ በመፈፀም፤ ብልሹ አሠራሮችና ሌብነትን በመታገል የህብረተሰቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በላቀ ደረጃ እንዲመለሱ በቀሪ ወራት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በገቢ አሰባሰብ፣ በልማት ፕሮጀክቶች አፈጻጸምና በቱሪዝም ዘርፍ የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን አመላክተዋል።
በውይይቱ የተሳተፉ በየደረጃው ያሉ አመራሮችም በቀጣይ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚተጉ አስታውቀዋል።