የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

የሸገር ከተማን 'ስማርቲ ሲቲ' እቅድ እውን ለማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

Apr 27, 2025

IDOPRESS

ሚያዚያ፤18/2017(ኢዜአ)፦የሸገር ከተማን 'ስማርቲ ሲቲ' እቅድ እውን ለማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባና አገልግሎት ክላስተር አስተባባሪ አቶ ጉግሳ ደጀኔ ገለጹ።


በሸገር ከተማ አስተዳደር ለሚቀጥሉት ሰላሳ ዓመታት ስራ ላይ የሚውል 'ስማርት ስቲ' ረቂቅ ፍኖተ ካርታ ላይ ያተኮረ ውይይት በቢሾፍቱ ከተማ ተካሄዷል።


በውይይቱ ላይ የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የሸገር ከተማ አስተዳደር የስራ ሀላፊዎች እንዲሁም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።


በውይይቱ መክፈቻ ላይ የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባና አገልግሎት ክላስተር አስተባባሪ አቶ ጉግሳ ደጀኔ፤ የከተማው 'ስማርት ሲቲ' ሀሳብ እና እቅድ እውን እንዲሆን የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።


ከዚህ ውስጥ ለሚቀጥሉት ሰላሳ ዓመታት ስራ ላይ የሚውለው የሸገር ከተማ 'ስማርት ሲቲ' ረቂቅ ፍኖተ ካርታ አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።


ይህ ሀሳብ እንዲሳካ ከተማ አስተዳደሩ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ካለፈው ዓመት ጀምሮ የመነሻ ጥናት ማካሄዱን ገልጸዋል።


መነሻ ጥናቱ ብዙ ጉዳዮችን ያጠቃልለለ መሆኑን አንስተው፥ ይህን መነሻ ሀሳብ መሰረት በማድረግ ለሰላሳ ዓመታት የሚተገበረው ረቂቅ ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን አስረድተዋል።


ረቂቅ ፍኖተ ካርታው በውስጡ ከተማው አሁን ያለበትን ሁኔታ መሰረት በማድረግ የህዝብ ብዛት፣ መሰረተ ልማቶች ያሉበት ደረጃ እና ወደፊት እንዴት መሆን እንዳለባቸው የሚያመለክቱ ሀሳቦችን መያዙን አንስተዋል።


በተጨማሪም የመሬት አጠቃቀም፣የቱሪዝም ልማትና ከብክለት የጸዳ የትራንስፖርት ሁኔታ እንዲኖር አቅጣጫ ጠቋሚ ሀሳቦችን ያከተተ መሆኑን ተናግረዋል።


በአጠቃላይ የሸገር ከተማ 'ስማርት ሲቲ' ረቂቅ ፍኖተ ካርታ ከሰላሳ ዓመታት በኃላ የሚሰጡ አገልግሎቶች ሙሉ በሙሉ በቴክኖሎጂ የታገዙ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው ብለዋል።


በብልጽግና ፓርቲ የሸገር ከተማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አለማየው ቱሉ በበኩላቸው፥ ሸገር ከተማ የህዝቡን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጥያቄዎች ለመመለስ ከተቋቋመ ጀምሮ የተለያዩ ጥረቶች እያደረገ ይገኛል ብለዋል።


በመሆኑም ፍኖተ ካርታው በዘላቂነት ተወዳዳሪ እና ዘመኑን የሚመጥን ከተማ ለማፍጠር ትልቅ እገዛ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።


ፍኖተ ካርታው የከተማ አስተዳደሩን የ10 ዓመት እቅድ፣የከተማዋን የምሥረታ ግብ እና ሌሎችንም ሀሳቦች መሰረት ተደርጎ የተዘጋጀ እንደሆነ አስታውሰዋል።


የውይይቱ ተሳታፊዎችም ረቂቅ የፍኖተ ካርታው ከተማውን በትክክለኛ መንገድ ለመምራትና የህዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያግዝ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.