ጋምቤላ፤ሚያዚያ 27/2017 (ኢዜአ)፦በጋምቤላ ክልል ያለው እምቅ ሃብት በማልማት ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉአላዊነትን በአጭር ጊዜ ማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን በብልጽግና ፓርቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለጹ።
በጋምቤላ ክልል በመገኘት ’’የድህረ እውነት ዘመን በእውነትና በእውቀት’’ በሚል መሪ ሐሳብ ለሚዲያና ኮሙኒኬሽን አመራሮችና ባለሙያዎች እየተሰጠ ያለውን የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና አስጀምረዋል።
ከዚሁ መርሃ ግብር በተጓዳኝም በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎችን ለሀገር እድገትና ብልጽግና ተስፋ ሰጭ ጅምሮች መሆናቸውን ተናግረዋል።
የጋምቤላ ክልል ገና ያልተነካ ሁሉን አብቃይ የሆነ ምድር እና የምርት አቅም ያለው መሆኑን ጠቅሰው፥ በክልሉ ያለው እምቅ ሃብት በማልማት ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉአላዊነትን በአጭር ጊዜ ማረጋገጥ የሚያስችል ነው ብለዋል።
የክልሉ እምቅ ሃብት የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥም ባለፈ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል የሚፈጥርና መሆኑን ገልጸው፥በተለይም በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን አድንቀዋል።
በተለይም በባለ ሃብቶች በስፋት እየለማ ያለውን የግብርና ስራ ልምድና ተሞክሮ በመጋራት የሁሉም አርሶ አደሮች ትኩረት እንዲሆን ማድረግ ይገባል ብለዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋትሉዋክ ሮን (ዶ/ር) በአካባቢው በተለይም የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት የላቀ ኢኮኖሚያዊና ስነ-ምህዳራዊ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በክልሉ በስፋት እየተከናወነ ያለው የአረንጓዴ አሻራ ልማትም ከተፈጥሮ ሃብትና የምግብ ዋስትና ጋር የተቆራኘ መሆኑን ጠቅሰው፥ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የጋምቤላ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አሺኔ አስቲን፤ በክልሉ ያለውን ጸጋ ተጠቅሞ ለሚሰራ ባለሃብትም ሆነ አርሶ አደር ውጤታማነት የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን እገዛና ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አንስተዋል።