ወራቤ፤ ሚያዝያ 28/2017(ኢዜአ)፦ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር) በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ የ5 ነጥብ 72 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ የአስፓልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ሥራ አስጀመሩ።
ለመንገዱ ዛሬ የመሰረት ድንጋይ ተቀምጦ ስራው በተጀመረበት ወቅት እንደተገለጸው የአስፓልት መንገዱ ከ1 ቢሊዮን 61 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቅ ነው።
የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቱ ወጪ በመንግስትና በህብረተሰቡ ተሳትፎ እንደሚሸፈንም ተመልክቷል፡፡
ፕሮጀክቱ በሁለት ዓመት ከ3 ወር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃም ተገልጿል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ የመንገዱን ግንባታ ሥራ ከማስጀመር በተጨማሪ በዞኑ ዳሎቻ ከተማ አስተዳደር በ194 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባውን የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል፡፡
የውሃ ፕሮጀክቱ ከ33ሺህ በላይ የአካባቢውን የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ያደርጋልም ተብሏል።
በምረቃ ሥነ ስርዓቱ ላይ የፌዴራል፣ የክልሉና የስልጤ ዞን ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡