አሶሳ፤ ሚያዝያ 28/2017(ኢዜአ):- ለኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ምላሽ በመስጠት የምስራቅ አፍሪካን የኢኮኖሚ ትስስርና የጋራ ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሚገባ ተገለጸ።
በፈጣን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገትና በቀጣናው የጋራ ተጠቃሚነትን እውን ለማድረግ የባህር በር እንዲኖራት የዲፕሎማሲ ጥረቷን አጠናክራ ቀጥላለች።
የባህር በር ባለቤት መሆን እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ግዙፍ ኢኮኖሚና በርካታ ህዝብ ላላቸው ሀገራት የወጪ እና ገቢ ንግድን በማሳለጥ ኢኮኖሚን በከፍተኛ ሁኔታ የሚደግፍ ከመሆኑም ባለፈ የጋራ ልማትን የሚያበረታታ ነው።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህሩ ሙሐመድ ኢብራሂም፤ ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት ለመሆን እያደረገች ያለው ጥረት ከራሷ አልፎ ለቀጣናው ሀገራት የምጣኔ ሃብት እድገትና የጋራ ተጠቃሚነት ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም ለኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ምላሽ በመስጠት የምስራቅ አፍሪካን የኢኮኖሚ ትስስርና የጋራ ተጠቃሚነት ማሳደግ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
የአንዱ ሀገር ተጠቃሚነት በሌሎች ሀገራት የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የራሱ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን አንስተው በተናጠል ማደግ የማይቻል በመሆኑ በተለይም በጎሮቤት ሀገራት መካከል ጠንካራ የኢኮኖሚ ትስስር መፍጠር ይገባል ብለዋል።
የባህር በር ጥያቄው ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ መሆኑንና ለቀጣናው ሀገራት ደግሞ በጋራ ተጠቃሚነትና አብሮ የማደግ የምጣኔ ሃብት ትስስርን ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ነው ያስረዱት።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ግዙፍ የኢኮኖሚ ባለቤት ለመሆን የያዘችውን ዕቅድ ለማሳካት የባህር በር ጉዳይ ቀዳሚ አጀንዳ መሆኑኑ ተገቢ እንደሆነም ነው በአፅንኦት የገለጹት።