ሰመራ፤ግንቦት 2/2017(ኢዜአ)፦በአፋር ክልል የአርብቶ አደሩ የኑሮ መሰረት የሆኑ እንስሳትን በመንከባከብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን የማጎልበት ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸው ተገልጿል።
በክልሉ ጭፍራ ወረዳ የተገነቡ የተለያዩ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችና የመኖ ልማት ስራዎች የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ አመራር አባላት በተገኙበት ዛሬ ተመርቀዋል።
በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፥ በክልሉ የአርብቶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያጎለብቱ ተግባራት ናቸው።
በዚህም የአርብቶ አደሩ የኑሮ መሰረት የሆኑ እንስሳትን በመንከባከብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ለማሳደግ ከሚያስችሉ ተግባራት መካከል የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችና የእንስሳት መኖ ልማት ስራዎች ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።
ለእንሰሳቱ የሚደረገው ድጋፍና እንክብካቤም የአርብቶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንደሚያጠናክርም አስረድተዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የመሬት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ ዑመር ኑሩ እንደተናገሩት በክልሉ ድርቅን ለመቋቋም የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ ነው።
በተለይም የአርብቶ አደሩን ተጋላጭነት ለመቀነስና ኑሮውን ለማሻሻል ከተሰሩ ፕሮጀክቶች መካከል በጭፍራ ወረዳ ላይ ተገንብተው ለምረቃ የበቁት የውሃና የመኖ ልማት ስራዎች ለአብነት እንደሚጠቀሱም ተናግረዋል።
በክልሉ አራት ወረዳዎች በተከናወኑ የልማት ተግባራት የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የገለፁት ደግሞ የክልሉ የእንስሳትና ዓሣ ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም መሐመድ ናቸው።
የጭፍራ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አሊ አርባ በበኩላቸው፥ ከለውጥ በኃላ በተሰሩ ስራዎች አርብቶ አደሩ ማህበረሰብን ደረጃ በደረጃ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አመልክተዋል።
አስተዳዳሪው አክለውም ከተመረቁት ፕሮጀክቶች መካከል በወረዳቸው ከሚገኝ ወንዝ በፀሐይ ኃይል በመታገዝ ውሃን በመጥለፍ የተከናወነው የእንስሳት መኖ ልማት ሊጠቀስ እንደሚችል ገልፀዋል።
በክልሉ በሚገኙ ደዌ፣ ተላላክ፣ አሚባራና ጭፍራ ወረዳዎች የተለያዩ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ ሲሆን ዛሬ ለምረቃ የበቁት በጭፍራ ወረዳ በሁለት ቀበሌዎች የተጠናቀቁት መሆናቸውም ተገልጿል።