አዲስ አበባ፤ ግንቦት 3/2017(ኢዜአ)፦ ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ብዝኃ ኢንቨስትመንትን በማስፋፋትና ለአርሶ አደሩ ዘላቂ የገበያ ትስስር በመፍጠር ተጨባጭ ውጤት እያመጡ መሆኑን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ገለጸ፡፡
በኢትዮጵያ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የመንግሥት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብና ጥራት የመፈጸም አቅም ጨምሯል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ምክትል ሥራ አስፈፃሚ ዘመን ጁነዲ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በኢኮኖሚ ዘርፍ በተደረገው ሪፎርም በአሰራር ደንብና መመሪያዎች ላይ መሰረታዊ ለውጥ ተደርጓል።
ሪፎርሙ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ማነቆዎችን በመፍታት ለዓለም አቀፍ አልሚዎች አስቻይ የኢንቨስትመንት አማራጭ እንዲፈጠር ማድረጉን ገልጸዋል፡፡
ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ካሏቸው 177 ሼዶች 150ዎቹ በሀገር ውስጥና በውጭ ባለኃብቶች መያዛቸውን ገልጸው፤ እንደ ጅማ፣ ባህርዳርና ሀዋሳ ያሉ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች አዳዲስ ኢንቨስትመንት እየሳቡ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
በዚህም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ባለፉት ዘጠኝ ወራት 80 አዳዲስ ኢንቨስትመንት ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ማስገባት መቻሉን ገልጸው፤ ይህም ከዕቅድ በላይ የተገኘ ውጤት ነው ብለዋል፡፡
በቴክስታይልና ጋርመንት ላይ ትኩረት ያደርግ የነበረውን አሰራር ወደ ብዝኃ ኢንቨስትመንት አማራጭ ማሸጋገርና ማስፋት መቻሉንም ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችን ካላቸው ነባራዊ ጸጋ ጋር በማዋሀድ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲሰራባቸው እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና የተጀመረው ሎጂስቲክስና ንግድ አዲስ እሳቤ መሆኑን ገልጸው፤ ብዝኃ ኢንቨስትመንትን በማሳለጥ የጎላ ሚና እንዳለውም ተናግረዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ማደጋቸው ብዝሃ ኢንቨስትመንትን ከመፍጠር ባለፈ ሰፊ የሥራ እድልና ትስስር እየፈጠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በሁሉም ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ከ85ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ከኢንዱስትሪዎች ጋር ቀጥታ በማገናኘት ዘላቂ የገበያ ትስስር ተፈጥሯል ብለዋል፡፡
ባለፉት ዘጠኝ ወራት በባህር ዳር ልዩ የኢኮኖሚ ዞን በግብርና ምርቶች ማቀነባበር ላይ የተሰማራ የውጭ ድርጅት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ፈሰስ በማድረግ ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
በጅማ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን አቮካዶ ምርትን በማቀነባበርና እሴት በመጨመር የተሰማራ ኩባንያ ብዝኃ ኢንቨስትመንትን ከማሳደግ ባለፈ ለአካባቢው ማህበረሰብ የሥራ እድልና የገበያ ትስስር ፈጥሯል ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀዳሚና ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እየሆነች ነው ያሉት ምክትል ሥራ አስፈፃሚው፤ በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ያለው የተሟላ መሰረተ ልማት የኢንቨስተሮችን ቀልብ መሳቡን ገልጸዋል፡፡
ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ከጨርቃጨርቅና አልባሳት ባሻገር ሌሎች የዓለም የትኩረት ዘርፍ በሆኑ የታዳሽ ሀይል ላይ በትኩረት እየሰሩ መሆኑንም ጨምረው አንስተዋል፡፡
በሀዋሳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን በሶላር ኢነርጂ ላይ የተሰማራ የውጭ ድርጅት 100 ሚሊዮን ዶላር ሀብት ያስመዘገበ ኩባንያ ሥራ መጀመሩን ጠቅሰው፤ ይሄውም ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተመዘገበ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡