ወልዲያ ፤ግንቦት 3/2017(ኢዜአ)፡- ለዘንድሮ የመኸር እርሻ ማዳበሪያ ወቅቱን ጠብቆ መቅረቡ ማሽላና ሌሎች ቀድመው የሚዘሩ ሰብሎችን ፈጥነው ለመዝራት እንዳስቻላቸው የሰሜን ወሎ ዞን አርሶ አደሮች ገለጹ።
የዞኑ ግብርና መምሪያ በበኩሉ ለ2017/18 የመኸር ወቅት የሚውል እስካሁን ድረስ ከ72 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ መከፋፈሉን አስታውቋል።
በዞኑ በጉባ ላፍቶ ወረዳ የአላውሃ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ወንድሙ ጎበና ለኢዜአ እንደገለጹት የዘንድሮው የማዳበሪያ አቅርቦት በጊዜ መሆኑ ካለፉት ዓመታት በተሻለ የዘር ወቅትን ለመጠቀም አስችሏቸዋል።
መንግሥት ዘንድሮ የአፈር ማዳበሪያ ቀድሞ እንዲደርሰን ማድረጉ ማሽላንና ሌሎች ቀድሞ የሚዘሩ ሰብሎችን ከወዲሁ ቀድመን ለመዝራት አስችሎናል ብለዋል።
አንድ ኩንታል ዩሪያና ዳፕ ማዳበሪያ ከአካባቢያቸው ህብረት ሥራ ማህበር በመግዛት በአንድ ሄክታር መሬታቸው ላይ ጥቅም ላይ እያዋሉ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
ሌላው የዚሁ ወረዳ አርሶ አደር ሲሳይ ዓለሙ ዘንድሮ ለበልግና ለመኸር እርሻ ማዳበሪያ ቀድሞ መድረሱ በልማቱ የተሻለ ተጠቃሚ ያደርገናል ብለዋል።
የማሽላ ዘር የሚዘራበት ወቅት ላይ መሆናቸውን ጠቁመው የማዳበሪያና የዝናብ ስርጭቱ የተስተካከለ መሆኑ ለምርታማነት ማደግ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
በሰሜን ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ የግብርና ግብዓቶች አቅርቦትና ስርጭት ባለሙያ አቶ ሳሙዔል ደሳለኝ በበኩላቸው፣ በዞኑ 217 ሺህ 634 ኩንታል ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ለማሰራጨት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
እስካሁን በተሰራው ስራም 72 ሺህ 313 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ከ62 ሺህ በላይ ለሚሆኑ አርሶ አደሮች መሰራጨቱን አስታውቀዋል።
ቀሪው ከጅቡቲ ወደብ እየተጓጓዘ መሆኑን ጠቁመው እስከተያዘው ወር አጋማሽ ድረስ አርሶ አደሩ እጅ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዞኑ በ2017/18 የኸመር ወቅት ከ231 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የሚለማ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 27ሺህ ሄክታሩ በአሁኑ ወቅት በማሽላ ዘር መሸፈኑን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።