አዲስ አበባ፤ ግንቦት 3/2017(ኢዜአ)፦ የኮሪደር ልማቱ መንግስት በአጭር ጊዜ ውስጥ ቃሉን በተግባር ያሳየበትና ለመዲናዋ ልዩ ውበት ያጎናጸፈበት ነው ሲሉ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ።
የኮሪደር ልማቱ የመዲናዋን ገጽታ በፍጥነት ከመቀየር ባሻገር ምቹ የመዝናኛ ስፍራና ተመራጭ እንድትሆን ያደረገ ነው።
በአዲስ አበባ ከተማ ከተገነቡት የመዝናኛ ስፍራዎች መካከል አራት ኪሎ፣ መገናኛ ቦሌና ፒያሳ ይገኙበታል።
ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ ወልደማሪያም ደግነቱ እንደገለጹት፤ መንግስት መዲናዋን ለመቀየር ያሳየው ተነሳሽነት በእጅጉ የሚደነቅ ነው።
ከ40 ዓመት በላይ ካዛንቺስን እንደሚያውቋት የሚገልጹት አቶ ወልደማሪያም፤ በአጭር ጊዜ አካባቢው ላይ የታየው ለውጥ የሚያስደስትና የሚያስደምም ነው ብለዋል።
መንግስት ለከተማዋ ውበት ትኩረት በመስጠት በተጨባጭ ያሳየው ለውጥ ቃልን በተግባር ለመተርጎም ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ እንደሆነም ጠቁመዋል።
አቶ አማኑኤል ሮዱሰን ልጃቸውንና ባለቤታቸውን ለማዝናናት እና የኮሪደር ልማቱን ለመጎብኝት ከቡራዩ አሊዶሮ አካባቢ መምጣታቸውን ይናገራሉ።
የመዝናኛ ቦታዎቹ ዋጋ የተከፈለባቸው፣ አእምሮን የሚያድሱ፣ የሚያስደስቱና በብልሃት የተገነቡ መሆናቸውን ለመመልከት መቻላቸውን ይገለጻሉ።
መዲናዋ ደረጃዋን በጠበቀና የነገ አገር ተረካቢ ትውልድን ታሳቢ ባደረገ መልኩ መገንባቷን መታዘባቸውን አቶ ወልደማሪያም ገልጸዋል።
የልማት ቦታዎቹ ከፍተኛ የሕዝብና የመንግስት ሃብት ወጥቶባቸው ስለተገነቡ በኃላፊነት ልንጠብቃቸውና ለመጪው ትውልድ ልናስረክባቸው ይገባል ያሉት ደግሞ አቶ አማኑኤል ናቸው።
ከአያት አካባቢ ልጆቻቸውን ለማዝናናት የመጡት አቶ ኤፍሬም ምስጋና በበኩላቸው፤ የኮሪደር ልማቱ እጅግ የሚያስደስት፣ ማራኪና የተዋበ ተደርጎ መገንባቱን መመልከታቸውን ይገልፃሉ።
የኮሪደር ልማት ቀጣዩ ትውልድ ብሩሕ አእምሮ ይዞ እንዲያድግ ለማድረግ እንደሚያስችል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
በፒያሳ በኮሪደር ልማት የተገነቡትን የመዝናኛ ስፍራዎች ለማየት የመጡት አቶ ዘውዱ መሳፍንት እና ባለቤታቸው ወይዘሮ መቅደስ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ የመዝናኛ ስፍራዎች እጅግ ሳቢ ናቸው ይላሉ።
የመዝናኛ ስፍራዎቹ ግንባታ ሕብረተሰቡ ንጹሕና ማራኪ በሆኑ ቦታዎች ጊዜውን እንዲያሳልፍ የሚያደርጉም እንደሆነ ነው የሚገልጹት።