አዲስ አበባ፤ ግንቦት 4/2017(ኢዜአ)፦ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን(ዶ/ር) ገለጹ።
ኮሚሽነሩ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት፥ የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት እምቅ ሀብቶች የማስተዋወቅ ስራ በስፋት ሲሰራ ቆይቷል።
ኢንቨስት ሊደረግባቸው የሚችሉ ዘርፎችን በማስተዋወቅ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ በተሰራ ስራ ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡንም ተናግረዋል።
በዘርፉ የተሻሻሉ ህጎች፣ አዋጆችና ደንቦች እንዲሁም የመንግስት ቁርጠኝነት ከፍተኛ ለውጥ እያመጡ መሆኑን ገልጸዋል።
መንግስት ትኩረት በሰጠባቸው የግብርና፣ ማዕድን፣ ቱሪዝም፣ ማኑፋክቸሪንግ እና አይሲቲ ዘርፎች በርካታ ባለሀብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ እየተሰራ ነው ብለዋል።
እንደኮሚሽነሩ ገለፃ የገቢና ወጪ ንግድ እንዲሁም የጅምላና ችርቻሮ ንግዱ ለውጭ ባለሀብቶች መከፈቱ ትልቅ ዕድል ፈጭሯል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ፈተናዎችን በመቋቋም እያንሰራራ እንደሚገኝም ኮሚሽነር ዘለቀ(ዶ/ር) ጨምረው ተናግረዋል።
በተለይም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መልካም ዕድል የፈጠረና እድገት እንዲመዘገብ ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች በተለያዩ መስኮች ኢንቨስት እያደረጉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለሚያደርጉ ባለሃብቶች የመንግስት ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።