ጋምቤላ፤ ግንቦት 4/2017(ኢዜአ)፦ ለክልሉ ህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የገቢ አቅማችንን ልናሳድግ ይገባል ሲሉ የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋትሉዋክ ሮን(ዶ/ር) ገለጹ።
በክልሉ የገቢ አቅምና የማህበረ-ኢኮኖሚ ጥናት ዙሪያ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የተሳተፉበት የውይይት መድረክ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተካሄዷል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋትሉዋክ ሮን(ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት የክልሉ ህዝብ ለሚያነሳቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች የተፋጠነ ምላሽ ለመስጠት የገቢ አቅምን ማሳዳግ ይገባል።
ክልሉ ሰፊ የተፈጥሮ ሀብቱንና የንግድ እንቅስቃሴው የሚያመነጨውን ገቢ በአግባቡ መሰብሰብ ከቻለ የመደበኛ ወጪዎችን በራስ አቅም መሸፈን እንደሚቻል ተናግረዋል።
ካሁን በፊት የክልሉን ገቢ አሟጦ መሰብሳብ ባለመቻሉ የልማት ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው የጊዜ ሰሌዳ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዳይበቁ ምክንያት ሆኖ መቆየቱን አስታውሰዋል።
በመሆኑም በክልሉ በገቢ አሰባሰብ በኩል የሚታዩ ተግዳሮቶችን በማስቀረትና የገቢ አቅምን በማሳደግ የህዝቡን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ ተግቶ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በተለይም በክልሉ የተካሄደውን የገቢ አቅምና የማህበረ-ኢኮኖሚ ጥናት ተግባራዊ በማድረግ የገቢ አቅምን ለማሳደግ በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አካላት በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የውይይት መድረኩ ዓላማ በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አካላት በገቢ አቅምና ማህበረ-ኢኮኖሚ ጥናቱ ዙሪያ የጠራ ግንዛቤ በመያዝ ለተግባራዊነቱ እንዲረባረቡ ለማስቻል ነው ብለዋል።
የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ ዴቪድ ሯች(ዶ/ር) በበኩላቸው የገቢ አቅምና የማህበረ-ኢኮኖሚ ጥናት ማካሄድ ያስፈለገው የክልሉን የገቢ አሰባሰብ በማሻሻል የህብረተሰቡን የልማት ፍላጎቶች ለመመለስ በማለም መሆኑን ገልጸዋል።
ዘላቂና ቀጣይነት ያለው የገቢ አሰባሰብ ስርዓት ለአንድ ሀገር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ዓይነተኛ ፋይዳ ያለው መሆኑን የገለጹት ደግሞ ከኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የክልሉን የገቢ ጥናት ሰርተው ያቀረቡት ሀገርቢገኝ ገብረመስቀል(ዶ/ር) ናቸው።
ስለሆነም የክልሉን ልማትና እድገት ለማፋጠን ዘላቂና ቀጣይነት ያለው የገቢ አሰባሰብ ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል ብለዋል።
በውይይት መድረኩ ከክልል እስከ ወረዳ የሚገኙ የአመራር አካላትና የዘርፉ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።