ሆሳዕና ፡ ግንቦት 6/2017 (ኢዜአ)፡-.በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት በተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች የህዝብን ችግር በዘላቂነት የሚፈቱ በመሆናቸው ሊጠናከሩ እንደሚገባ አስተያየታቸውን የሰጡ የክልሉ ነዋሪዎች ገለጹ ፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ግንባታቸው እየተከናወኑ ከሚገኙ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች የተጠናቀቁትን መርቀው አገልግሎት እያስጀመሩ ይገኛሉ፡፡
ነዋሪዎቹ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በአካባቢያቸው የተገነቡት የመንገድ፣ የውሃና ሌሎች የመሰረተ ልማት ስራዎች የነዋሪውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ ናቸው።
በክልሉ በምስራቅ ጉራጌ ዞን ደቡብ ሶዶ ወረዳ ሜልኮ ኩሉንዴ ቀበሌ ነዋሪዋ ወይዘሮ ትዕግስት አየለ እንዳሉት አገልግሎት መስጠት የጀመረው የሜልኮ ጉምባርናዳ መንገድ ከዚህ ቀደም የነበረባቸውን ዘርፈ ብዙ ችግር የፈታ ነው።
ከሰሞኑ ተመርቆ ወደ አገልግሎት ከገቡት ውስጥ በሀዲያ ዞን አን ሌሞ ወረዳ የተገነባው የ15 ኪሎ ሜትር የገጠር መንገድ አንዱ ሲሆን በወረዳው የከቤቾ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ተማም ፉሉሴ የመንገድ ግንባታው ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለው ገልፀዋል፡፡
በስልጤ ዞን የዳሎቻ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ በይዳ ሁሴን በበኩላቸው በንጹህ መጠጥ ውሃ እጥረት ሳቢያ ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ሲዳረጉ መቆየታቸውን አስታውሰው አሁን ችግሮቹ እንደተፈቱም ገልፀዋል፡፡
መንግስት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች እያከናወናቸው የሚገኙ የመሰረተ ልማት ስራዎችን አጠናክሮ እንዲቀጥል የጠየቁት ነዋሪዎቹ የአካባቢውን ማህበረሰብ ችግር ለመፍታት እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ ቁርጠኛ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በበኩላቸው በክልሉ የህዝብን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግና ፈጣን ዕድገትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ በርካታ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ በትኩረት እየተከናወነ ይገኛል፡፡
ግብርናን ለማሳለጥ የሚያስችሉ የመስኖ አውታሮች፣ በክልሉ ክላስተር ማዕከላት 165 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት፣ የጤና ተቋማትና የማህበረሰብ መድኃኒት ቤቶችን አካቶ 90 የተለያዩ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተፋጠነ መሆኑንም አክለዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅሰው ነዋሪዎች የልማት ስራዎችን በመደገፍና በጥንቃቄ በመጠቀም ፈጣን እድገት እንዲረጋገጥ አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል ፡፡