ደሴ ፤ ግንቦት 7/2017(ኢዜአ )፡-የዲጂታል ቴክኖሎጂ መስፋፋት የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማሳደግ የላቀ ትርጉም እንዳለው ተገለጸ።
ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ለቢራሮ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የኮምፒውተር፣ የራውተር እና ነጻ የኢንተርኔት አገልግሎት ድጋፍ አድርጓል።
በዚሁ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መሀመድአሚን የሱፍ፤ ኩባንያው ላደረገው ድጋፍ አመስግነው እገዛው ለመማር ማስተማር ሥራው አጋዥ መሆኑን ገልጸዋል።
የዲጂታል ቴክኖሎጂ መስፋፋት በተለይም ለትምህርት ጥራትና ተደራሽነት የላቀ ትርጉም እንዳለው አንስተዋል።
በተለይ በዲጂታል ዘመን ትምህርት ቤቶችን በቴክኖሎጂ በማጠናከር ብቁና ተወዳዳሪ ትውልድ ማፍራት ጊዜ የሚሰጠው አይደለም ብለዋል።
በከተማው የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን በማዘመን የትምህርት ጥራትን ለመጠበቅ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዛሬ ያደረገው ድጋፍ ትምህርት ቤቶችን በቴክኖሎጂ ለማጠናከር የሚሰራውን ስራ እንደሚያግዝም አስታውቀዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መንግስቱ አበበ በበኩላቸው፣ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በቴክኖሎጂ ታግዞ የሚሰጥ መሆኑን አስታውሰው ድጋፉ ለዚህ ከሚኖረው ፋይዳ ባለፈ ለተማሪዎች ቅድመ ልምምድ እንደሚያግዝ አስረድተዋል።
የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ሪጅናል ውጭ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሲሳይ ዘሪሁን በበኩላቸው ዲጅታል ኢትዮጵያን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ኩባንያው የበኩሉን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።
ለዚህም ከ60 ለሚበልጡ የመንግስት 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ድጋፍ ማድረጋቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
በዛሬው እለትም በኮምቦልቻ ከተማ ለሚገኘው ቢራሮ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 10 ዘመናዊ ኮምፒውተር፣ ሁለት ራውተር እኛ የ6 ወር ያልተገደበ ነጻ ኢንተርኔት ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
ቀጣይም በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች ድርጅቱ መስል ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።